Fana: At a Speed of Life!

ዘመናዊና ሃይል ቆጣቢ ዲጂታል የመብራት ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ

ሲግኒፋይ ከብሉ ስፓርክ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ልዩ የፊሊፕስ ስማርት ላይት ማሳያ ማዕከል በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ በይፋ ከፍቷል፡፡

ማዕከሉ የባለሙያዎችን ሙያዊ ምክርና ዘመን አፈራሽ የመብራት ቴክኖሎጂዎችን ከኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች እና ነጋዴዎችጋር እንደሚያቀራርብ ተመላክቷል፡፡

ለቤት ባለቤቶች፣ ለሕንጻ ንድፍ ባለሙያዎች፣ ለዲዛይነሮችና ለሕንጻ ተቋራጮች፣ የፊሊፕስ የመብራት ምርቶችን የቦታ አቀማመጥ እንዲመለከቱ፣ እንዲያወዳድሩና ለፍላጎታቸው የሚስማማውን እንዲመርጡም ያስችላል፡፡

በመክፈቻ መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ መንግሥት ምክትል አምባሳደር ፓውላ ሽንደለር እና ሌሎች የንግድ አጋሮች፣ ነጋዴዎች፣ አርክቴክቶች እና ዲዛይነሮች ተገኝተዋል፡፡

በቤታቸው ዘመናዊ፣ ለዓይን ምቹ፣ኃይል ቆጣቢ እና የግል የአኗኗር ዘይቤን የሚገልጽ መብራት ለሚመርጡ ሰዎች ማዕከሉ የተለያዩ የፊሊፕስ የመብራት ምርቶችን፣ በእውነተኛ የክፍል አቀማመጦች የተዘጋጁ ማሳያዎችንና የባለሙያዎችን የምክር አገልግሎት በአንድ ሥፍራ ያቀርባል።

በመብራት ዘርፍ ዓለም አቀፍ መሪ በሆነው ሲግኒፋይ ኩባያ የመካከለኛው ምሥራቅ፣ አፍሪካ እና ፓኪስታን የደንበኞችና የንግድ ሥራ ገበያ መሪ የሆኑት ማኖጅ ጃያቻንድራን እንዳሉት÷ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ በፍጥነት እያደጉ ካሉ ኢኮኖሚዎች አንዷ ናት፤ ይህንንም በመላው አዲስ አበባ እየተገነቡ ባሉ አዳዲስ ቤቶች፣ አፓርታማዎችና የቢሮ ሕንፃዎች ላይ በግልጽ ማየት ይቻላል።

ስለሆነም ማዕከሉ ለቤት ባለቤቶችና ለነጋዴዎች የዘመናዊ መብራትን ተሞክሮ በተጨባጭ ያቀርባል፤ ደንበኞች የሚያምሩ የመብራት ዕቃዎችን ከዘመናዊ አምፖሎች ጋር በስልካቸው አገናኝተው መጠቀም ይችላሉ ብለዋል፡፡

በማዕከሉ ውስጥ ጎብኚዎች ዘመናዊ የብርሃን አጠቃቀምን በቀጥታ መሞከር፣ የብርሃን መጠንን መቀነስና መጨመር፣ ለእራት፣ ለጥናት ወይም ለመዝናናት የተለያዩ የብርሃን ሁኔታዎችን ማዘጋጀት፣ እንዲሁም መብራቶች በራሳቸው እንዲበሩና እንዲጠፉ ሰዓት መመደብ እና ሌሎች መሰል ተግባራትን በቀላሉ ከስልካቸው በቀጥታ ማድረግ ይችላሉ።

የብሉ ስፓርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ መኮንን ታደሰ በበኩላቸው÷የፊሊፕስ ልዩ የማሳያ ማዕከል ስንከፍትርዕያችን ምርቶችን እና አገልግሎታቸውን በአንድ ሥፍራ ከማሳየት የሚሻገር መሆኑን በሚገባ ለማሳየት ነው ብለዋል።

ከመብራት ዲዛይንና ከምርት ምርጫ አንሥቶ እስከ ተከላ ድረስ፣ ልዩ ማዕከሉ አጠቃላይ የመብራት ልምድን በአንድ መድረክ ላይ ያቀርባል ነው ያሉት፡፡

ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ክፍት በሚሆነው ማሳያ ማዕከሉ ውስጥ ጎብኚዎች ኦሪጅናል የፊሊፕስ ምርቶችን ከብሉ ስፓርክ በአካባቢያዊ ዋስትና እና ከሽያጭ በኋላ በሚሰጥ ድጋፍየመግዛት ዕድል እንዳላቸው ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.