Fana: At a Speed of Life!

የማያንቀላፋው ክንደ ብርቱ፡ የታጋሹ ጋሻ ወሰንና የላኪዎች ቀቢጸ-ተስፋ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰላምን ውድ ዋጋ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ የስልጣኔና የታሪክ አርማ የሆነ የሀገር አለኝታ ነው።

ይህ ግዙፍ ሠራዊት ውሳኔዎቹንና አቋሞቹን የሚቃኘው በታጠቀው ሃያል ወታደራዊ አቅምና የኃይል የበላይነት ልክ ሳይሆን፣ እንደ አንዲት ታላቅና ታሪካዊት ሀገር ጥልቅ አርቆ አሳቢነት ነው።

ኢትዮጵያ ሰላምን የምትመርጠው ከፍርሃት ወይም ከርምጃ አቅም ማነስ ሳይሆን የሰላም ፍሬ ለቀጣናው ሕዝቦች የሚያስገኘውን ዘላቂ በረከት ከልብ ስለምታስብ ነው።

ታሪክ ግን አሁንም ሕያው ምስክር ነው፡፡ ትናንት የሻዕቢያ ቡድን በባድመ በኩል የከፈተውን እኩይ ወረራ በብረት ክንዱ ቀልብሶ፣ የጠብ አጫሪዎቹን ወረራ ከስሩ ለመንቀልና ለጠማቂዎቹ የሚገባቸውን ታሪካዊ ዋጋ ሊሰጣቸው ወደ አስመራ እየገሰገሰ ባለበት ወቅት በትዕዛዝ እንዲመለስ ተደርጓል።

ሆኖም ግን ሻዕቢያ ዛሬም ያንን የቅርብ ጊዜ የሽንፈት ታሪክ የረሳው ይመስላል። የኢትዮጵያ ሠራዊት ለሰላም ሲባል የሚያሳየውን «የማያንቀላፋ ክንደ-ብርቱ ዝምታ» እንደ ድክመት የሚቆጥር፣ የፖለቲካ ብስለት የጎደለው ስብስብ ሆኖ ቀጥሏል።

ዛሬም የፈርኦኖች የጥፋት ተላላኪነት አይኑን ያሳወረው ይህ ተቸካይ ቡድን በሀገራችን ድንበርና መረጋጋት ላይ መተናኮሱን አላቆመም።

በገዛ እጁ ለመግጠም ወገቡ ስለሚያጥር፣ በተላላኪዎቹ በኩል እኩይና የጥፋት አጀንዳዎቹን ለመፈጸም ይደክማል። ነገር ግን ላኪዎችም ሆኑ ተላላኪዎች አንድ ትልቅ እውነታን ሊረዱት ይገባል፡፡

ለሰላም ሲባል ዝምታን የመረጠው የኢትዮጵያ መከላከያ ጋሻ፣ የትዕግስቱ ጽዋ የሞላች ዕለት የሚያወርደው የፍትሕ ክንድ ለተላላኪዎች ብቻ ሳይሆን ለዋናዎቹ ላኪዎችም የሚፋጅ እሳት ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ትዕግስቷ ሰፊ፣ ይቅር ባይነቷ የጠለቀ ቢሆንም ሉዓላዊነቷና ብሔራዊ ደህንነቷ መስመር ሲያልፍ ግን እጁን አጣጥፎ የሚመለከት አቅም የላትም።

የትዕግስት ወሰን ሲነካ የሚነሳው የኢትዮጵያ ክንድ፣ የቀጣናውን የኃይል ሚዛን እንደገና የሚያስተካክል የታሪክ አውሎ ነፋስ መሆኑን ትናንት ያላወቁት ዛሬ ሊረዱት ይገባል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.