2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ የስኳር እጥረት እንዳይከሰት 2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ተገዝቶ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚኖረውን ከፍተኛ የስኳር ፍላጎት ለማሟላትና የአቅርቦት እጥረት እንዳይገጥም 2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ግዥ ተፈጽሞ ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ላይ መሆኑን በሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ገልፀዋል።
መሰረታዊ የምግብ ምርት የሆነው ስኳር በሀገር ውስጥ እየተመረተ ለህብረተሰቡ የሚሰራጭ ሲሆን ፍላጎቱ ከአቅርቦቱ በላይ በሚሆንበት ጊዜ ከውጪ ተገዝቶ እየመጣ የሀገሪቱን የሥኳር ገበያ የማረጋጋት እና ህብረተሰቡ የሚያስፈልገውን የስኳር መጠን እንዲያገኝ ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሆነ ተገልጿል።
በስኳር ኮርፖሬሽን የአቅርቦት ክትትልና ዌር ሀውስ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ተሰማ በበኩላቸው ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ላይ ያለው ስኳር እንዳለ ሆኖ ለቀጣይ ሁለት ወራት ፍጆታ የሚሆን በቂ ስኳር በክምችት ስላለ እጥረት አይገጥመንም ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ነገር ግን ህገ-ወጥ ነጋዴዎችና ደላሎች ምርት በመሸሸግ፣ ዋጋ እንዲጨምር እና ገበያው እንዲረበሽ በማድረግ እጥረት እንዲፈጠር ሊያደርጉ ስለሚችሉ ህግ የማስከበር ስራ ይሰራል ሲሉ አቶ ወንድሙ ተናግረዋል፡፡