ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በባንክና ፋይናንስ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በባንክ እና ፋይናንስ ዘርፍ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት እና ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ሀገራት ስማምነቱ ላይ የደረሱት በታይላንድ ባንኮክ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን በተካሄደ የሁለትዮሽ ውይይት ነው።
በስብሰባው ላይ የተሳተፈውን የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ማዕከላዊ ባንክ ገዥ ካሊድ መሐመድ ባላማ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም የሁለቱን ሀገራት የፋይናንስ ሥርዓቶች ይበልጥ ማቀራረብ፣ የልምድ ልውውጥ ማድረግ እና በባንክና ፋይናንስ ዘርፍ ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ሀሳቦችን መለዋወጣቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።