ባለአደራ አስተዳደሩ በቀዳሚነት ሕዝባዊ አገልግሎቶችን የማነቃቃት ሥራዎችን ይተገብራል – ከንቲባ ሽሻይ አማረ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል የፌደራል መንግሥት የባለአደራ አስተዳደር ሕዝባዊ አገልግሎቶችን የማነቃቃት ሥራዎችን በቀዳሚነት ይተገብራል አሉ የመቐለ ከንቲባ ሽሻይ አማረ (ዶ/ር)።
ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ትግራይ ክልልን የሚያስተዳደረው ባለአደራ አስተዳደሩ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ የግዛት አንድነትና የትግራይን ሕዝብ መሠረታዊ ጥቅሞች መሠረት በማድረግ እንደሚሰራ ይጠበቃል፡፡
በባለአደራ አስተዳደሩ የመቐለ ከንቲባ ሆነው የተሾሙት ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የህገወጡ ህወሓት ቡድን የጥፋትና የቁማር ፖለቲካ አብቅቷል።
የተቋቋመው ባለአደራ አስተዳደር ቀዳሚ ተግባሩ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን መሰረታዊ የሕዝብ አገልግሎቶችና የመሰረተ ልማት ስራዎችን ማጠናከር መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን ተግባር በብቃት ለመወጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ቀያቸው መመለስና ኢኮኖሚን ማነቃቃትም ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የትግራይ ክልል ሕዝብ ዴሞክራሲ ስርዓት፣ እኩልነትና ፍትህን ለማረጋገጥ ለረጅም ጊዜ ዋጋ ከፍሏል ያሉት ከንቲባው፤ በቀጣይም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ሕዝቡ በመረጠው መንግሥት እንዲተዳደር ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ አንስተዋል፡፡
በዚህም ለቀጣይ ምርጫ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ኃላፊነታቸውን በሚገባ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ የባለአደራ አስተዳደሩ ተልዕኮውን ለመፈፀም ከሕዝቡና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋገጠዋል።