የሀገር መከላከያ ሠራዊት ታማኝነትና የህዝብ ክብር
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጊዜያት ሲቀያየሩ ሀገር በዘላቂነት ትቀጥላለች፤ እንደ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ያሉ የህዝብን ጥቅም የሚያስከብሩ ተቋማትም በወቅቶች የሚለዋወጡ ሳይሆን፤ የሀገር ዳር ድንበርና ሉዓላዊነትን እያስጠበቁ ይቀጥላሉ፡፡
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊገዳደሩ የመጡ የውጪም የውስጥም ፈተናዎች በተገቢው መንገድ፣ በድል የተመለሱት በመከላከያ ሠራዊት ብርቱ ክንድ ነው፡፡
የመከላከያ ሠራዊት ለሀገር ህልውና ምሰሶ ነው፣ የሀገሪቱን ነጻነት በደምና በአጥንት አስጠብቀው ላቆዩ አባቶች አደራ የታመነ፣ ዘመናዊነትን በተላበሰ መንገድ ራሱን በቴክኖሎጂ አዘምኖ ያስቀጠለ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከተለያዩ አካባቢዎችና ማንነቶች የተወጣጣ በጋራ የመስራት፣ የወንድማማችነት ምልክትና የህብረብሔራዊነት ተምሳሌት ነው፡፡
የሀገር ሉዓላዊነትና የህዝብን ሰላም በማስከበር ረገድ እስከ መስዋዕትነትና ራስን አሳልፎ እስከ መስጠት ድረስ ይታመናል፡፡
መከላከያ በጦርነት ጊዜያት ብቻ የተገደበ እንቅስቃሴ ሳይሆን፤ ይልቁን ማህበረሰቡን ማገዝ በተገባው ጊዜ ሁሉ ከፊት ይቀድማል፤ በተለያዩ ተግባራትም የህዝብ ልጅነቱን አሳይቷል፡፡
አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ለተጎዱ አካባቢዎች የምግብና የውሀ ድጋፎችን በመስጠት፣ በሰብል ስብሰባ በማገዝ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለማህበረሰቡ ያለውን ድጋፍ አሳይቷል፡፡
በየዓመቱ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ላይ ችግኞችን በመትከል ለአየር ንብረትና የውሃ ጥበቃ ተሳትፎዎችን በማድረግ ከወታደራዊ ተግባራቱ ጎን ለጎን ተፈጥሮን የመጠበቅ ተግባራትን ያካሂዳል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ ስፖርተኞችን በማፍራትና የኢትዮጵያን ባህል በተለያዩ መድረኮች በማስተዋወቅ ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡
እነዚህ ሁሉ የመከላከያ ሠራዊት የሀገር ዳር ድንበርን ከመጠበቅ ጎን ለጎን የሚያስኬዳቸው ተግባራት ከህዝብ ጋር የቀረበ እንዲሆን ተጨማሪ አቅም ፈጥረዋል፡፡
ከህዝብ የወጣና ለህዝብ ለሚሰራው የመከላከያ ሠራዊት አክብሮትና ድጋፉን ሊገልጽ ማህበረሰቡ በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በነቂስ በመውጣት ድጋፉን አሳይቷል፡፡
ይህም የኢትዮጵያ ህዝብ ያከበረውንና ሀገሩን ያስከበረለትን ሁሉ ማክበርን እንደሚያውቅና ክብር ለሚገባቸው ሁሉ ክብርን እንደሚሰጥ ያሳያል፡፡
በቤተልሔም ግርማ