Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በዓለም ባንክ የ22 የአፍሪካ ሀገራት ተወካይ ሆና ተመረጠች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8 ፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)ኢትዮጵያ 22 የአፍሪካ ሀገራትን በሚወክለው የዓለም ባንክ ቡድን የአፍሪካ ምድብ አንድ ተወካይ ሆና ተመረጠች።

የምድቡ ሀገራት ብሔራዊ ባንክ ገዥዎች አቶ ሳንዶካን ደበበ ኢትዮጵያን እና ምድቡን በመወከል በቦታው እንዲሰየሙ ያቀረቡትን ሹመት ያረጋገጡ ሲሆን ይፋዊ የሥራ ዘመናቸውም ከፈረንጆቹ 2026 ህዳር 1 የሚጀምር ይሆናል።

ምድብ አንድ አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ቡሩንዲ፣ ኤርትራ፣ እሰዋቲኒ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋምቢያ፣ ኬንያ፣ ሌሶቶ፣ ላይቤሪያ፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ሩዋንዳ፣ ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ፣ ሲሼልስ፣ ሴራሊዮን፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳን ያካተተ ስብስብ ነው።

ይህ ሹመት ኢትዮጵያ በዓለም ባንክ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛውን የቦርድ አመራር ቦታ ለማግኘት የቻለችበት ሦስተኛው አጋጣሚ ነው።

አቶ ሳንዶካን ደበበ ቀደም ሲል በዚህ ኃላፊነት ላይ የነበሩትን ሁለቱን አንጋፋ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ (ከ1972 እስከ 1974 እ.ኤ.አ) እና ወ/ሮ ሙሉ ከተማን (ከ2006 እስከ 2008 እ.ኤ.አ) በመከተል ነው ይህንን አህጉራዊ ኃላፊነት የሚረከቡት።

ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ትልቁ የዓለም ባንክ የልማት ፕሮጀክትና ፋይናንስ ፖርትፎሊዮ ካላቸው ሀገራት አንዷ በመሆኗ፣ በባንኩ የፋይናንስ፣ የፖሊሲ አቅጣጫ እና የልማት ቅድመ አጀንዳዎች ላይ ከፍተኛ ድርሻ አላት።

በመሆኑም ይህ ኃላፊነት ኢትዮጵያ በዓለም ባንክ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የአፍሪካን ድምፅ ለማጠናከር ትልቅ እድል ይሰጣታል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.