ባለፈው አንድ ሳምንት ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ግምታዊ ዋጋቸው ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ከነሐሴ 21 እስከ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት ቀናት በተለያዩ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢዎች መያዛቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
በተጨማሪም በብሔራዊ ባንክ ፍቃደ ያላገኘ 2000 የአሜሪካን ዶላር በመንገደኛ እጅ ተገኝቶ የተወረሰ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡
ለግለሰብ የማይፈቀዱ እና ለሀገር ደህንነት ስጋት የሆኑ ካሜራ የተገጠመላቸው ሰዓት፣ መነፅርና በድብቅ የሚቀርፁ የግድግዳ ካሜራዎች እንዲሁም የስናይፐር ክፍሎች በቦሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ወደ ሀገር ለማስገባት ሲሞከር ተይዘዋል፡፡
በህገወጥ መንገድ ከሶማሌላንድ በቶጎውጫሌ አድርጎ ሊገባ የነበረ ግምታዊ ዋጋ ያልወጣለት መጠኑ 4 ነጥብ 5 ኪ.ግ የሆነ ማዕድን ተይዟል፡፡
ከተጠቀሰው ጠቅላላ ግምታዊ ዋጋ ውስጥ 12 ሚሊየን ብር የሚገመተው በህገ-ወጥ መንገድ የጉምሩክ ክልልን በመግባታቸው በጋላፊ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የተያዙ ተለያየ ሞዴል ያላቸው አምስት ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በፍተሻ፣ ጫካ እና ቤት ውስጥ ተከማችተው በጥቆማ ተደርሶባቸው፣ በከባድ ጭነት ተሽከርካሪ ባለ 40 ጫማ ባዶ ኮንቴነር ውስጥ ተደራቢ ላሜራ በውስጥ በኩል በማዘጋጀት ባዶ ኮንቴይነር በማስመሰል ለማለፍ ሲሞከር እንደሆነ ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
እንዲሁም የተያዙት ዕቃዎች የህዝብ ጤንነት እና ሰላም አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ ህጋዊ የንግድ ውድድርን የሚያዛቡ የጦር መሳሪያዎች፣ መድኃኒቶች፣ አደንዛዥ እፆች፣ ኤሌክትሮኒክሶች፣ የተሽከርካሪ ጎማ እና ልዩልዩ ምርቶች ናቸው፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በተያያበት ወቅት በዝውውሩ እጃቸው ሊኖርበት ይችላል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል ተብሏል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ 5 ሚሊየን ብ በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ሲጋራ እና ሺሻ የነዳኝ መኪና ታንከር ውስጥ በመደበቅ ለማሳለፍ ሲሞከር በአዋሽ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት መያዙን መረጃው አስታውሷል፡፡