Fana: At a Speed of Life!

ከእርዳታ ጥገኝነት ወደ ላኪነት፡ የኢትዮጵያ ግብርና አዲስ ምዕራፍ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በለመለመ አፈር፣ በእልፍ ወንዞች እና ሰፊ ለእርሻ የሚሆን መሬት ሀብት የታደለች ሀገር ናት። ይሁን እንጂ የዚህች ሀገር የዘመናት የግብርና ታሪክ ሲነበብ፣ ከለም መሬቷ ይልቅ በተረጂነት ጥላ ሥር የኖረችበት ጊዜ በሰፊው ይጻፋል።
የውጭ እርዳታን ጠባቂ በመሆን ያሳለፈችው ዘመን የፈጠረው ጠባሳ ከባድ ቢሆንም፣ ዛሬ ላይ የዚያ ታሪክ ምዕራፍ ተዘግቶ አዲስ የብልጽግና ታሪክ እየተጻፈ ይገኛል።
በመንግሥት ቁርጠኛ አመራርና አነሳሽነት በዘርፉ የተመዘገበው ለውጥ፣ የሀገሪቱን ግብርና ከወቅታዊ የዝናብ ጥገኝነት አላቆ ወደ ታላቅ የልማት አብዮት አሸጋግሮታል። በመላ ሀገሪቱ በተከናወኑ የመስኖ ልማት ሥራዎች፣ አርሶ አደሩ ከበጋ እስከ በጋ ማምረት የሚያስችለው አቅም ተፈጥሯል።
ከዚህ ጎን ለጎን እየተስፋፋ የመጣው የኩታገጠም እርሻ አሠራር የባለሙያዎችን ድጋፍ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምንና የግብዓት አቅርቦትን በማቀናጀት የምርት መጠንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳደግ አስችሏል።
አርሶ አደሮች በተበታተነ መልኩ ከሚያደርጉት ልማዳዊ አሠራር ወጥተው በጋራ ማልማታቸው፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪ የሚሆን ግብዓት እንዲገኝ አድርጓል።
የኢትዮጵያን የግብርና ትራንስፎርሜሽን በግልጽ ከሚያሳዩት ድንቅ ስኬቶች መካከል የስንዴ ልማት ይጠቀሳል። ከዓመታት በፊት በሚሊየን የሚቆጠር ኩንታል ስንዴ ከውጭ ሀገራት በዕርዳታና በግዢ ስታስገባ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ በራሷ አቅምና መሬት ላይ በመተማመን ድል አስመዝግባለች።
በቆላማ አካባቢዎች ጭምር በመስኖ በተከናወነው የስንዴ ልማት የሀገሪቱን ፍላጎት ከማሟላት አልፎ፣ ለጎረቤት ሀገራት በመትረፍ ወደ ዓለም ገበያ መላክ ተጀምሯል። ዘመናዊ እሳቤዎች ዘርፉን ከባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ወደ ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂ መር ሥርዓት አሸጋግረውታል።
የተሻሻሉ ዘሮችን መጠቀም፣ ማዳበሪያን በአግባቡ ማስተዋወቅ፣ እና እንደ ትራክተርና ኮምባይነር ያሉ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን የማስፋፋት ሥራዎች ተሰርተዋል። ይህም የሰው ኃይል ድካምን ከመቀነሱም በላይ የምርት ጥራት እንዲጠበቅ አድርጓል።
ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ግብርና ከእጅ ወደ አፍ ከነበረ የድህነት መታወቂያው ወጥቶ፣ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ የኢኮኖሚ ምሰሶ መሆኑን አረጋግጧል። ስንዴን ጨምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ እና የቅባት እህሎች ምርት ለዓለም አቀፍ ገበያ እየቀረቡ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ዛሬ ከምግብ እርዳታ ጥገኝነት በመላቀቅ የግብርና ምርቶችን ለገበያ እያቀረበች ሲሆን ከዚህ ባሻገር የአፍሪካ የምግብ ማዕከል የመሆን ተስፋዋን እውን ለማድረግ እየገሰገሰች ትገኛለች።
በመልካም ፈቃዱ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.