Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በጎርፍ ምክንያት ለተፈናቀሉ ከ177 ሺህ በላይ ዜጎች የሰብአዊ እርዳታ የመስጠት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ በጎርፍ ምክንያት ለተፈናቀሉ ከ177 ሺህ በላይ ዜጎችን የሰብአዊ እርዳታ የመስጠት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የብሄራዊ የአደጋ ስጋትና አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ለፋና ብሮካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፀውበክረምቱ ከመደበኛ በላይ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ እስከ አሁን በሰባት ክልሎች ጉዳት አድርሷል።

የብሄራዊ አደጋ ስጋት እና ስራ አመራር ኮሚሽን መረጃ እንደሚለው መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ የሚጥለው ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ አስከትሎ ዜጎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ቅድመ ትንበያ 3 የስጋት ማስጠንቀቂያ ሪፖርቶችን አውጥቷል።

የኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክተር ወይዘሮ አልማዝ ደምሴ ከፋና ብሮድካስቲነግ ኮርፖረቴት ጋር በነበራቸው ቆይታም፥ ክረምቱን ተከትሎ በሚጥለው ዝናብ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይቷል ብለዋል።

እስከ አሁንም ለኮሚሽኑ በተደረገለት ሪፖርት በጎርፍ ምክንያት በመላው ሀገሪቱ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 177 ሺህ ተሻግሯል።

ሰሞኑን በተለይ በኦሮሚያ እና አፋር ክልሎች ጎርፍ ባስከተለው ጉዳት ለተፈናቀሉ ዜጎች ፈጣን ምላሽም እየተሰጠ ነው ።

የኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስጋት እና ስራ አመራር ኮሚሽንን አቶ ገረመው ኦሊቃ፥ የወንዞች ሙላት እና የቆቃ ገድብ ሞልቶ መፍሰስ ባስከተለው ጎርፍ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መጠለያ የማመቻቸትና ምግብ የማቅረብ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው የሚሉት።

ጎርፉ በአከባቢው ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የሚናገሩት ኮሚሽነሩ፤ አሁንም አስጊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን አስቀድሞ ከአከባቢው እንዲነሱ ጥረቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።

ከመደበኛ በላይ እየጣለ ያለው ዝናብ የወንዞች ሙላትን አስከትሎ እየደረሰ ያለው ጎርፉ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስም ከአከባቢው ማህበረሰብ ጋር ጭምር በቅንጅት መሰራቱም ይቀጥላል ብለዋል።

ለጎርፍ ቅድመ መከላከል ስራ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መድቦ ወደ ስራ በገባው የአማራ ክልልም እየጣለ ያለው ዝናብ ጉዳት አድርሷል።

በክልሉ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የአደጋ ስጋት ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክተሩ አቶ ጀምበሩ ደሴ እንደተናገሩት፥ በምስራቅ እና ምእራብ የክልሉ አከባቢዎች ጎርፍ በሰብል ላይ ጭምር ከፍተኛ ጉዳትን አስከትሏል።

በዚህ ምክንያትም ለተፈናቀሉ ዜጎች የመድረስ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ።

እየጣለ ያለው የክረምት ዝናብ አሁንም ተጠናክሮ በመቀጠሉ የጎርፍ ስጋቶች እንዳሉ የሚያስረዳው ደግሞ የብሄራዊ ሜትሪዮሎጂ ኤጀንሲ ነው።

የኤጀንሲው የአየር ሁኔታ እና ትንበያ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫሊ ደበሌ፥ በክረምቱ መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እየተመዘገበ ቀጥሏል።

ከባድ ዝናብ የሆነ ከ30 እስከ 110 ሚሊ ሜትር መጠን በቀን ጭምር መመዝገቡን በማንሳት፤ ይህም ሁኔታ በቀጣይ ቀናት እና በመስከረም ወርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ትንበያዎች ያመላክታሉ ብለዋል።

ይህ ደግሞ ወደ ጎርፍ የመቀየር ሰፊ እድል እንዳለው የተናገሩት ዳይሬክተሯ፥ የመሬት መንሸራተት እና መሰጠንቅን ጭምር ሊያስከትል እንደሚችል ይናገራሉ።

ህዝቡም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል።

የብሄራዊ አደጋ ስጋት እና አመራር ኮሚሽን በበኩሉ የዝናብ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎች ለጎርፍ ተጋላጭ ይሆናሉ፤ ከእነዚህም 434 ሺህ ሰዎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ ሲል ግምቱን አስቀምጧል።

በሀይለየሱስ መኮንን

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.