የድሮን ምርምርና ልማትን ለማጠናከር የሚያግዝ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የስካይዊን ኤሮናቲክስ ኢንዱስትሪና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የድሮን ምርምርና ልማትን ለማጠናከር የሚያግዝ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
በሁለቱ ተቋማት መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ የኢትዮጵያን የኤሮናቲክስ ቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ፣ የድሮን ምርምርና ልማትን ለማጠናከር እንዲሁም የአየር ላይ ቅየሳ አገልግሎትን ለማስፋፋት ያለመ ነው፡፡
ስምምነቱ በድሮን ዲዛይንና ምርት እንዲሁም በሥርዓት ሙከራና ለማረጋገጥ፣ በሰው ኃይል ልማትና በቴክኖሎጂ ትብብር ለመፍጠር፣ ልምድና ዕውቀትን በመለዋወጥና የምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባራዊ መፍትሔዎች ለማሸጋገር እንዲሁም የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ አቅምን ለማሳደግ እድል እንደሚፈጥር ተመላክቷል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ስምምነቱ የሁለቱን ተቋማት አቅም በማቀናጀት የምርምር ውጤቶችን ወደ ተጨባጭ ምርትና አገልግሎት ለማሸጋገርና የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል።
የኤሮናቲክስና የድሮን ቴክኖሎጂዎች በተለያዩ የልማት ተግባራት ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው በማንሳት የተቀናጀ አመራር መስጠት ለትብብሩ ስኬት ወሳኝ በመሆኑ በፍጥነት ወደ ትግበራ መገባት እንዳለበትም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የሰነዱ መፈረም ለሀገር በቀል የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና ለአቪዬሽን ዘርፉ እድገት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የትብብሩን አስፈላጊነት ያጎላል ብለዋል።
የሀገር ውስጥ የኤሮስፔስ ዘርፍ እድገትን ለመደገፍ ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸው ይህም ከተቋማዊ ግንኙነት ባለፈ እንደ ሀገር በቴክኖሎጂ ራስን ለመቻል፣ የምህንድስና እውቀትን ለማስፋፋትና ለዘላቂ ልማት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት መግለጻቸውን የየብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ ያመለክታል።
ትብብሩ በሰነድ ደረጃ ብቻ ሳይገደብ፣ በፍጥነት ወደ ተግባር በመሸጋገር ተጨባጭና ዘላቂ ውጤት እንዲያመጣ ትኩረት በመስጠት እንደሚሠሩ የገለጹት ደግሞ የስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን ጓዴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡