በመዲናዋ ወደ ግማሽ ሚሊየን የሚጠጉ ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች ተላልፈዋል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት 5 ዓመታት የለውጥ እሳቤን እውን በማድረግ 496 ሺh 971 ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች ማስተላለፍ ተችሏል አለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር።
አስተዳደሩ ባለፉት አምስት ዓመታት የነዋሪዎችን መሰረታዊ ፍላጎትና አንገብጋቢ የሆነውን የቤት ችግር በመረዳት አዲስ የለዉጥ እሳቤን እዉን በማድረግ 496 ሺህ 971 ቤቶች ተገንብተዉ ለነዋሪዎች እንዲተላለፉ ተደርገዋል::
ከተማ አስተዳደሩ እንዳለው÷ በቤት ግንባታ ልማት ሂደት ዉስጥ የመንግሥት ሚና ቀዳሚ በማድረግ የተለያዩ የግንባታ አማራጮችን በመዘርጋት ቤት አልሚ ሪል እስቴቶች፣ የግል አልሚዎች ህብረት ሥራ ማህበራት፣ እና በጎ ፈቃደኞች ተቀናጅተዉ በመኖሪያ ቤት ልማት ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ተፈጥሯል፡፡
የአጭር ጊዜ እቅዶችን በመንደፍና ተግባራዊ በማድረግ ስኬታማ ሥራዎችን በመተግበር ላይ እንደሆነና በዘንድሮው ሩብ ዓመት ብቻ የመርካቶ በጎነት መንደርን ጨምሮ ከ4 ሺ 200 በላይ ቤቶች በመገንባት ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ መቻሉን ገልጿል፡፡
እነዚህ የቤት ግንባታዎች ንጹህ የመኖሪያ አካባቢን የፈጠሩ መሆናቸውን ያነሳው ከተማ አስተዳደሩ ምቹ አካባቢ በመፍጠር የልጆች መጫወቻ የተሰራላቸው፣ ሰው የሚንቀሳቅስባቸው እና የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከሪያ ስፍራ የተሟላላቸው የዜጎችን ክብር የሚመጠኑ መኖሪያ መንደሮች ናቸው ብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልማት ተነሺዎችን፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸዉን፣ አረጋዉያንን፣ የሀገር ባለዉለታዎችን እና ሌሎች ቤት ፈላጊዎችን የቤት ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አካታች የሆነ የልማት ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ እንደሚገኝ የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡