Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የንግድ ማጭበርበሮችን የሚከላከል የኪው አር ኮድ ምስጢራዊ የደረሰኝ ሕትመት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በተሳሳተ ደረሰኝ የሚከናወኑ የንግድ ማጭበርበሮችን መከላከል የሚያስችል ባለ ኪው አር ኮድ ምስጢራዊ የደረሰኝ ሕትመት ተጀምሯል።

የባለ ኪው አር ኮድ (QR Code) ምስጢራዊ የደረሰኝ ሕትመት ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን ፈንታው በዚሁ ወቅት ፥ የሕትመት አሠራሩ ለዝግጅት ይወስድ የነበረውን ጊዜና ወጪ ከመቆጠብ ባሻገር የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማዘመንና ከአጭበርባሪዎች በመጠበቅ የታቀደውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ምስጢራዊ ሕትመቱ በደንበኞች በኩል ይነሱ የነበሩ የጥራትና የጊዜ ቅሬታዎችን ሙሉ በሙሉ የሚመልስ እንደሆነ አስተድተዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ካሣሁን ደመመ በበኩላቸው ፥ አዲሱ አሠራር የሐሰተኛ ደረሰኞችን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በመግታትና የተደራሽነት ችግርን በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል።

ፋብሪካው ምስጢራዊነቱ የተጠበቀ የደረሰኝ ሕትመት አገልግሎት መጀመሩ ደንበኞች በጊዜና በጥራት ለከፈሉበት ዋጋ ትክክለኛ ደረሰኝ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ያለው ፋይዳ የጎላ ነው ያሉት ደግሞ የዓባይ ሕትመት እና የወረቀት ፓኬጅንግ ፋብሪካ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ታደሰ መላሽ ናቸው።

በደሳለኝ ቢራራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.