የአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በአፍሪካውያን የጋራ ውሳኔ ይጸናል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ የውይይት መድረክ ብቻ ሳይሆን፤ የአህጉሪቱን የፖለቲካ ትብብር ወደ ተግባር፣ የጋራ ርዕይን ወደ ተጨባጭ ውጤት እንዲሁም የሕዝቦቿን ተስፋ ወደ እውነታ የሚቀይር ታሪካዊ ዕድል ነው።
የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ከነበረው የሥልጣን ፉክክር ባሻገር የሕዝቦቻቸውን ጥቅም፣ የአህጉሪቱን ነፃነትና የትውልዶችን የወደፊት ዕድል ቅድሚያ የሚሰጡትም ጉዳይ ነው።
የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ መካሄዱ አህጉሪቱ ከሚገጥሟት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የአስተዳደር ተግዳሮቶች አንጻር ትርጉም ያለው የውይይት ዕድልን ይፈጥራል።
በፖለቲካ ቅኝት ሲታይ፣ ጉባኤው የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞችን ወደ የጋራ የአህጉራዊ ጥቅም ማምጣት፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህልን ማጠናከርና በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ በተቋማዊ ተጠያቂነትና በኢኮኖሚያዊ ትብብር ላይ የጋራ አቅጣጫዎችን ለመፈለግም ያግዛል።
አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ድምፅና ተደራዳሪነት ለማጠናከር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሀገራዊ ፉክክር ባሻገር ለአህጉራዊ ጥቅም በጋራ መሥራታቸው ወሳኝነቱ የማያከራክር ነው።
ይህም የአፍሪካን የወደፊት ዕድገት በውጭ ኃይሎች ፍላጎት ብቻ ሳይሆን በአፍሪካውያን የጋራ ራዕይና ውሳኔ ላይ ለመመሥረትም በር ከፋች ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በአፍሪካ የዴሞክራሲ ግንባታ፣ የሕዝብ ውክልና፣ የመንግሥት አስተዳደርና የልማት ፖሊሲዎች ቀረጻ ውስጥ ወሳኝ ሚና አላቸው።
የዜጎችን ፍላጎትና ምኞት ወደ ፖሊሲ በመቀየር፣ በምርጫ ሂደት በመሳተፍና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ ድምፅ በመሆን ለፖለቲካዊ ተሳትፎ መሠረት ይጥላሉ።
በአፍሪካ ያሉ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት በምርጫ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፤ የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት፣ የዜጎችን መብት ማክበር፣ ወጣቶችና ሴቶች በውሳኔ ሰጪነት እንዲሳተፉ ማበረታታት፣ ተጠያቂነትን ማጠናከርና ለሁሉም ዜጎች የሚጠቅም ዘላቂ ልማት ላይ መሥራትም ከዋነኞቹ ተግባራቸው መካከል ይገኙበታል።
በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ (APPS 2026) የፖለቲካ አመራር ለአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ለውጥና ዘላቂ ልማት ያለውን ሚና ለመመርመር የተዘጋጀ መድረክ ነው።
እንዲህ አይነቱ አህጉራዊ መድረክ ዋነኛ ጠቀሜታው የፖለቲካ ፓርቲዎች በልማት፣ በዴሞክራሲ፣ በአካታች አስተዳደርና በአህጉራዊ ትብብር ዙሪያ ልምድ እንዲለዋወጡና የጋራ መፍትሔዎችን እንዲፈልጉ ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ነው።
የአፍሪካ የወደፊት ዕድገት በተፈጥሮ ሀብቷ ብቻ ሳይሆን፣ በተጠያቂ አመራር፣ በጠንካራ ተቋማት፣ በዜጎች ተሳትፎና በትብብርም ይወሰናል።
አፍሪካ በሌሎች የሚቀረጽላት አህጉር ሳትሆን፣ የራሷን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በራሷ የምትቀርጽ አህጉር እንድትሆንም መሰል ጉባኤዎች ወሳኝ ናቸው።
2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ በአዲስአበባ ይካሄዳል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ