የወጣቶች አስተዋጽኦ የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት ወሳኝ ነው – አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የወጣቶች ሐሳብ እና አስተዋጽኦ የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት ወሳኝ ነው አሉ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር)።
2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ “እድገትን ማስተዳደር፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍሪካ ኢኮኖሚ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ንድፍ አውጪዎች ናቸው” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ዕለት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መካሄድ ጀምሯል፡፡
በዚህ አህጉራዊ መድረክ ላይ ሚኒስትሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ የፓርላማ አባላት፣ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ወጣቶችና ሴቶች፣ የልማት አጋሮች ተወካዮችና ዲፕሎማቶች እየተሳተፉ ነው፡፡
በጉባኤው የዛሬ ውሎ የአፍሪካ የሴቶች የፖለቲካ አመራር ጉባኤና የወጣቶች የፖለቲካ መድረክ እየተካሄደ ነው።
አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) በመድረኩ እንዳሉት፤ ከአፍሪካ ሕዝብ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ናቸው።
የአህጉሪቱ የልማትና የብልጽግና ጉዞ ወጣቶችን በማሳተፍና በማብቃት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ወጣቶች ፈጣሪዎች፣ የቢዝነስ አንቀሳቃሾች፣ የሰላም ገንቢዎችና የለውጥ ሀዋርያዎች በመሆናቸው ለአህጉራዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።
የወጣቶችን አቅም ለማጎልበት በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎችና በአመራር ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ አመልክተው፤ የወጣቶች መሪነት ነገ ሳይሆን ዛሬ ጭምር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ከ50 በመቶ በላይ የአመራር ቦታዎች በወጣቶች መያዛቸውን ጠቅሰው፤ ወጣቶች ዕድል ሲሰጣቸው የለውጥ ቀያሽ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ልምድ በግልጽ እንደሚያሳይ አንስተዋል።
ወጣቶችን ማብቃት በፖሊሲና በስትራቴጂ ሰነዶች ብቻ ሳይገደብ፣ ወጣቶችን እንደ መሪዎች በመቀበልና ኃላፊነት በመስጠት መተግበር እንዳለበት አመልክተዋል።
የወጣቶች ሐሳብ እና አስተዋጽኦ የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ወጣቶችን በመተማመን እኩል አጋሮች አድርጎ መመልከት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በመሳፍንት ብርሌ