የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ አሰባሰብና አጠቃቀም በሕግና ደንብ ሊመራ ይገባል – ማህሙድ አሊ ዩሱፍ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ አሰባሰብና አጠቃቀም በሕግና ደንብ ሊመራ ይገባል አሉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፡፡
2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ “እድገትን ማስተዳደር፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍሪካ ኢኮኖሚ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ንድፍ አውጪዎች ናቸው” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ሊቀመንበሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በአፍሪካ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ የሰላምና ልማት ግንባታ እንዲሁም አካታች
የፖለቲካ ምኅዳርን ለማጠናከር ሕብረቱ በቁርጠኝነት ይሰራል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሥልጣን ማግኘት ባለፈ ለሕዝብ የሚጠቅሙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችን የመቅረጽና ሀገራዊ ጥቅምን በተመለከተ የሕዝብን ግንዛቤ የማሳደግ ሰፊ ተልዕኮ እንዳለባቸው አብራርተዋል።
በተጨማሪም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመንግሥትን ተግባራት መከታተልና መቆጣጠር ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መርሆዎች መካከል እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
መንግሥታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የመጠበቅ፣ ነፃና ተዓማኒነት ያላቸውን ምርጫዎች የማካሄድና መሠረታዊ ነፃነቶችን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡
በፖለቲካ አካላት መካከል በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አለመግባባት ሲፈጠርም በውይይት መፍትሔ መፈለግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ጉባኤውን በማስተናገዷ ምስጋና አቅርበው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) የፖለቲካ አመራር፣ የለውጥ ሥራዎችና ርዕይ አድንቀዋል።
በመሳፍንት ብርሌ