በኮሮና ቫይረስ የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚደገፉበት ፕሮጀክት በመኩራ ደረጃ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰላም ሚኒስቴር ከሰባት የሲቪክ ማህበራት ጋር በመተባበር በኮቪድ 19 በሽታ የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተደረገበት ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡
ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ለሚገኙ 1 ሺህ 640 የማህበረሰብ ክፍሎች የምግብና የቁሳቁስ ተጠቃሚ የሚደረግበት ነው።
በወረዳዎቹ ለአራት ወራት በሙከራ ደረጃ የሚተገበረው ፕሮጀክት፣በቀጣይ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ይስፋፋል ተብሏል።
የሚኒስቴሩ የሰላም ግንባታ ዳይሬክተር ወይዘሮ አልማዝ መኮንን የሰላም ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስ በዜጎች የኑሮ ሁኔታና ሥነ ልቡና እያደረሰ ያለውን ጫና ለመቀነስ ፕሮጀክቶችን ነድፎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሲቪክ ማህበራት የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት በጥናት የተደገፈ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባቸው ወይዘሮ አልማዝ ማሳሰባቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የፕሮጃይኒስት ድርጅት ዋና ዳይሬክተርና ፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወይዘሮ ነፃነት መንግስቱ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚሆነው በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙና በቀን ገቢ ለሚተዳደሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በቀጣይ በአዲስ አበባከተማ በሚገኙ ወረዳዎችና በሌሎች በሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚስፋፋም ተናግረዋል።