Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር ወሳኝ ምዕራፍ ደርሷል – ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገው ድርድር ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል አሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ያስሚን ወሀብረቢ።

8ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት የሥራ ቡድን ስብሰባ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ተካሂዷል።

የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት ዋና ተደራዳሪ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ያስሚን ወሀብረቢ የተመራው የልዑካን ቡድን በጉባኤው ላይ ተገኝቶ አግባብነት ያላቸውን ውይይቶች አካሂዷል።

ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፥ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገው ድርድር ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

የድርጅቱ አባልነት ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር አካል እና ቅድሚያ ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት አንዱ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል መሆን የፖሊሲ ቀጣይነትን እና ግልጸኝነትን ከማጠናከሩም በላይ፤ ምርትና ምርታማነትን፣ የውጭ ንግድን እና ኢንቨስትመንትን በማስፋት ከፍተኛ የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።

ሚኒስትሯ ከባለብዙ ወገን ስብሰባው ጎን ለጎን ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የተካሄደው የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድር እጅግ ፍሬያማ ነበር ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

አክለውም እስካሁን ለሁለትዮሽ ድርድር ጥያቄ ካቀረቡ 17 ሀገራት መካከል ከ11ዱ ጋር ስምምነት ተፈርሟል ነው ያሉት።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
#fanamediacorporation

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.