የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ ረገድ ኢትዮጵያ የበኩሏን እየተወጣች ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የበካይ ጋዝ ልቀት መጠንን በፍጥነት በመቀነስ ረገድ ኢትዮጵያ የበኩሏን ኃላፊነት እየተወጣች ትገኛለች አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
በቱርክዬ አንታሊያ ከተማ ‘ከቃላት ባለፈ ወደ ተግባርና አፈጻጸም መሸጋገር’ በሚል መሪ ሃሳብ 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ31) እየተካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጉባኤው ባደረጉት ንግግር፤ የአየር ንብረት ለውጥ በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ዘርፏን በጽኑ መሠረት ላይ እየገነባች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የንፋስ፣ የፀሐይ እና የጂኦተርማል ኃይል ልማቶችን ከማስፋፋት ባለፈ የኑክሌር ኃይልን ለማልማት አቅዳ እየሠራች እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ማኅበረሰቡ ለከባድ የአየር ንብረት ክስተቶችና አደጋዎች አስፈላጊውን ዝግጁነት እንዲያደርግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።
በዚህም ለአርሶ አደሮች አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ለመስጠትና የአየር ሁኔታ ትንበያን ለማሻሻል የሳተላይት መረጃዎችን እንዲሁም የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉን አመልክተዋል።
በተጨማሪም የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ድጋፍ የሚሹ ቤተሰቦችን በፍጥነትና በቀላሉ ለመድረስ አጋዥ መሆኑን ገልጸው፤ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ውጤታማ የሚሆነው አስቸኳይ ምላሽ የመስጠት አቅም ሲኖር እንደሆነ ተናግረዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ ማግኘት በሀገራት መካከል ካለው ፉክክር ባሻገር ጠንካራ ዓለም አቀፍ ትብብር ይጠይቃል ብለዋል።
የወደፊት የጋራ ዕጣ ፈንታችንን በምን መልኩ ፋይናንስ ማድረግ እንዳለብን ራሳችንን በቁርጠኝነት መጠየቅ ይገባናል ሲሉም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ቁርጠኛ ርምጃ መውሰዷን ገልጸው፤ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ በመከልከል ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የመሸጋገር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ከፍተኛ ኃላፊነትና አቅም ያላቸው አካላት የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በምታሰናዳው ኮፕ32 ላይ ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ አሠራሮችን በማዕከልነት በማስቀመጥ፣ ለአየር ንብረት አደጋዎች በይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ አካላት የገንዘብ ድጋፍ ቅድሚያ እንዲደርስ ትሰራለች ብለዋል።
ለዚህ ስኬትም ኢትዮጵያ ከኮፕ31 ፕሬዚዳንት ጋር በቅርበት እንደምትሠራ አረጋግጠዋል።
በዮናስ ጌትነት