Fana: At a Speed of Life!

በታዳሽ ኃይል ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ በሆኑት የንጹሕ ኃይልና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ በልዩ ትኩረት እየሰራች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ እነዚህን በጥብቅ የተሳሰሩ ቁልፍ መስኮች ለማልማት በቂ የተፈጥሮ ሀብትና አስቻይ ሁኔታዎችን የታደለች መሆኗ ስትራቴጂያዊ ዕድል ነው።

አካታች የኢኮኖሚ ልማትን እውን ለማድረግ ታዳሽ ኃይል የልማት መሠረት ሲሆን፤ የዲጂታል መሠረተ ልማት ደግሞ ሞተር በመሆን ሂደቱን ያሳልጣል፡፡

ሀገሪቱ በዚህ ማዕቀፍ ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ባለፈ የዓለም አቀፍ ዲጂታል ኢኮኖሚ ተወዳዳሪና ፈጣሪ የመሆን ራዕይን ለማሳካት ያስችላታል።

እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ኃይል የማመንጨት አቅም እያሳደጉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ 95 በመቶ ያህሉን የኤሌክትሪክ ኃይል የምታገኘው ከታዳሽ ኃይል ምንጮች ነው፡፡

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂና ግዙፍ የመረጃ ማዕከላት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል በሚፈልጉበት በዚህ ወቅት፤ ኢትዮጵያ ያላት ተመጣጣኝና ከካርቦን ልቀት የጸዳ ኃይል ለቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪዎች ወሳኝ መሠረት ይሆናል።

ይህን ንጹሕ ኃይልን በመጠቀም ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራን ያጠናቀቀች ሲሆን፤ አሁን ላይ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አማካኝነት የቴሌኮም አውታሮችን፣ የ5ኛ ትውልድ ኔትዎርክ እና አረንጓዴ የመረጃ ማዕከላትን እያስፋፋች ትገኛለች።

የንጹህ ኃይልና ዲጂታላይዜሽን ቅንጅት የውጭና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፣ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን (ስታርትአፕ) ያበረታታል እንዲሁም ዜጎች ተመጣጣኝና ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀዳሚ የዲጂታል ማዕከል የመሆን ርዕይዋን ሙሉ በሙሉ እውን ለማድረግ የኃይል መሰረተ ልማቶችን የማዘመን፣ የኃይል ምንጭ ስብጥሩን የማብዛት ሥራ እያካሄደች ትገኛለች።

ከውሃ፣ ነፋስ፣ ጂኦተርማልና የጸሀይ ኃይል በተጨማሪ ከኒውክሌር ኃይል ለማመንጨት ወደ ሥራ ገብታለች፤ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን የማዘመን ሥራዎችም እየተካሄዱ ነው፡፡

ዜጎች የዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው የ5 ሚሊየን ኮደርስ ፕሮግራምን ጨምሮ ልዩ ልዩ ስልጠናዎች የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱም የዲጂታል ጉዞው አካል ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር የራቁ የገጠር አካባቢዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ አነስተኛ የሶላር ኃይል ማመንጫዎችን የማስፋፋት ሥራ እየተካሄደ ሲሆን፤ ይህም የዲጂታል አገልግሎትን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል፡፡

የኢትዮጵያን ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል አቅም በፖሊሲ ከተደገፈ የዲጂታላይዜሽን ጥረት ጋር በማስተሳሰር ፈጣን የኢኮኖሚ ሽግግርን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.