የሞሐመድ ቢን ዛይድ የሰብዓዊነት ፋውንዴሽን በአፍሪካ ሀገራት ተንቀሳቃሽ የዓይን ሕክምና አገልግሎት አስጀመረ
የሞሐመድ ቢን ዛይድ የሰብዓዊነት ፋውንዴሽን በአፍሪካ ገጠራማ አካባቢዎች ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች የዓይን ሕክምና አገልግሎትን ለማዳረስ የተንቀሳቃሽ ክሊኒክ ፕሮግራም መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡
የፕሮግራሙ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በሞሮኮና ሞዛምቢክ የተካሄደ ÷ ከሁለቱም ሀገራት የጤና ሚኒስቴሮች ጋር በትብብር ይተገበራል።
በቀጣይም የጤና አገልግሎት ለማግኘት በርቀትና በሌሎች ተግዳሮቶች ምክንያት የሚቸገሩ ማኅበረሰቦች ወደሚኖሩባቸው ሌሎች ሀገራት እንደሚስፋፋ ተመልክቷል።
በፕሮግራሙ የዓይን ምርመራ፣ የበሽታ ምርመራና ሕክምና እንዲሁም የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን÷ በመጀመሪያዎቹ 6ወራት በሁለቱ ሀገራት ወደ 15 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የመንግሥት ሚኒስትር ሼክ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን እንዳሉት÷ ሀገራቸው በፕሬዚዳንት ሼክ ሞሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን አመራርና የቀድሞው መሪ ሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያን ሰብዓዊ ቅርስ ተነስታ ለጤና አገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ለመድረስ ቁርጠኛ ናት።
ከሞሮኮና ሞዛምቢክ መንግሥታት ጋር በመተባበርም የተንቀሳቃሽ ክሊኒኮቹ የሕክምና አገልግሎትን በቀጥታ ገጠራማ አካባቢዎች ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች በማድረስ ርቀት ለሕክምና እንቅፋት እንዳይሆን ያግዛሉ ብለዋል።
በዓለም ዙሪያ ቢያንስ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ሰዎች የዓይን የማየት እክል እንዳለባቸው የተገለጸ ሲሆን÷ አብዛኞቹ በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ይኖራሉ።
ከእነዚህም ቢያንስ አንድ ቢሊየን የሚሆኑት በተገቢው የዓይን ሕክምና አገልግሎት እጥረት ምክንያት ሊከላከል ወይም ሊታከም የሚችል የማየት ችግር አጋጥሟቸዋል።
የዓይን የማየት እክል በግለሰቦች ጤና ላይ ብቻ ሳይሆን በትምህርት፣ በሥራ፣ በገቢ ማግኘትና በራስ ገዝነት ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል።
በተቃራኒው የዓይን ሕክምና የማየት ችሎታን በመመለስ የትምህርት፣ የሥራና የማኅበራዊ ተሳትፎ ዕድሎችን ያሰፋል። በዓይን ጤና ላይ የሚደረግ አንድ ዶላር ኢንቨስትመንት እስከ 28 ዶላር የሚደርስ የኢኮኖሚ ትርፍ ሊያስገኝ እንደሚችልም ተመላክቷል።
የሞሮኮ የጤናና ማኅበራዊ ጥበቃ ሚኒስትር ዩንስ ቢጂጁ÷ ሀገራቸው በንጉሥ ሞሐመድ ስድስተኛ አመራር የጤና ሥርዓቷን በማጠናከር ሁሉም ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ሳይገደቡ የጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እየሠራች መሆኑን ገልጸዋል።
ከፋውንዴሽኑ ጋር የተጀመረው ትብብርም የዓይን ሕክምናን ወደ ገጠር ማኅበረሰቦች በማቅረብ የበሽታ ምርመራና ሕክምናን በወቅቱ ለማዳረስ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
የሞዛምቢክ የጤና ሚኒስትር ኡሴኔ ሂላሪዮ ኢሴ በበኩላቸው÷ የጤና ፕሮግራም ስኬት የሚለካው በታካሚዎች ሕይወት ላይ በሚያመጣው ለውጥ መሆኑን ገልጸው÷ ዜጎች ረጅም ርቀት ሳይጓዙና ለሕክምና ሳይዘገዩ የዓይን ምርመራና ሕክምና እንዲያገኙ መንግሥታቸው እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል።