Fana: At a Speed of Life!

በሕገወጡ ህወሓት ፈርሶ የነበረውን የክልሉን ካቢኔ አቋቁመን ሥራ አስጀምረናል – አቶ አሰፋ አብርሃ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የአስተዳደርና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ አቶ አሰፋ አብርሃ በሕገወጡ ህወሓት አማካኝነት ፈርሶ ተበትኖ የነበረውን የክልሉን ካቢኔ አቋቁመን ሥራ አስጀምረናል አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትግራይ ባለአደራ አስተዳደር ጋር የክትትል ግምገማ ውይይት አካሂደዋል።

አቶ አሰፋ አብርሃ ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ባለአደራ አስተዳደሩ በመጀመሪያ 45 ቀናት ለማከናወን የያዛቸውን ዕቅዶች መፈጸሙን ገልጸዋል።

በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የፈረሰውን የክልሉን አስተዳደር እንደገና አደራጅቶ የማቋቋም ሥራ መሰራቱን አንስተው፤ የዞን፣ የወረዳ እና የቀበሌ አመራር እና መዋቅር መቋቋሙን ተናግረዋል።

በሕገወጡ ህወሓት አማካኝነት ፈርሶ ተበትኖ የነበረውን የክልሉን ካቢኔ አቋቁመን ሥራ አስጀምረናል ብለዋል።

የባለአደራ አስተዳደሩ በሰራው ሥራ በጀት ይዞ አቅዶ መስራት የሚችል ቁመና ያለው አደረጃጀት ተፈጥሯል ነው ያሉት።

ሥራ መስራት የሚችል እና ኃላፊነት የሚሰማው የሰው ኃይል መመደቡን ገልጸው፤ በቀጣይ የተመደበው የሰው ኃይል ሥራውን በአግባቡ እየተወጣ ስለመሆኑ የተጠናከረ ግምገማ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

የፍትህ፣ የፖሊስ እና የሚሊሻ አደረጃጀት እንዲመለስ መደረጉንም ጠቅሰው፤ ከዚሁ ጎን ለጎን በወንጀል ድርጊት ተፈርዶባቸው ከማረሚያ ቤት የወጡ የሕግ ታራሚዎችን በማደን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በመደረጉ በከተሞች አካባቢ ተባብሶ የነበረውን ሕገወጥ ድርጊት መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።

የባለአደራ አስተዳደሩ በሚቀጥለው ጊዜ ሶስት ነገሮች ላይ በትኩረት እንዲሰራ አቅጣጫ መቀመጡን አንስተው፤ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ላይ ህብረተሰቡን ለመደገፍ የተከማቸ እህል በአፋጣኝ እንዲሰራጭ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው፤ ይህም በትኩረት የሚፈጸም መሆኑን ተናግረዋል።

በመጨረሻም በክልሉ የተሳካ ምርጫ ተደርጎ ኃላፊነቱን በህዝብ ለተመረጠ መንግሥት ማሸጋገር የባለአደራ አስተዳደሩ የትኩረት አቅጣጫ ነው ብለዋል።

የፌዴራል መንግሥት የባለአደራ አስተዳደሩ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ እንደሆኑ መገምገሙን የገለጹት አቶ አሰፋ፤ የፌዴራል መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጦልናል ነው ያሉት።

በአቢይ ጌታሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.