Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት የቀጣናውን የኃይል ሚዛን ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከራሷ አልፎ የቀጣናውን የኃይል ሚዛን ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና አውለ አሉ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የመካከለኛው ምሥራቅና የእስያ ፓስፊክ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ አንተነህ ጌታቸው (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ለቀይ ባሕር አካባቢ ሀገራት በሰጥቶ መቀበል መርህ አብረን እንልማ ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

የቀይ ባሕር ጉዳይ የመሬት ብቻ ሳይሆን የአየር ጭምር መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በምድርም በሰማይም ተዘግቶባት ሰላም የሚሰፍንበት ቀጣና እና አህጉር እንደማይኖርም ሲሉ ማስገንዘባቸው አይዘነጋም።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ አስመልክተው አንተነህ ጌታቸው (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት የህልውና ጉዳይ መሆኑ ሁሉም የሚስማማበት ነው።

ኢትዮጵያ ካላት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የምታስመዘግበው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና የህዝብ ብዛት አንጻር የባህር በር የግድ ያስፈልጋታል ብለዋል።

የቀጣናው ተለዋዋጭነትና በአካባቢው ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለማስቀጠል የባህር በር ባለቤትነት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ደረጃ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጉልህ አስተዋጽኦ አላት ያሉት አንተነህ ጌታቸው (ዶ/ር) ከታሪክ፣ ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ባህል አንፃር ከባህር በር ዝግ ልትሆን አይገባትም ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከራሷ አልፎ ቀጣናዊ የኃይል ሚዛኑን ጠብቆ ለማቆየት ወሳኝ ጉዳይ ነው ማለታቸውን የዘግበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.