ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኮረና ቫይረስ የመመርመርያ ኪት ማምረቻ ፋብሪካ በይፋ መርቀው ከፈቱ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ የኮረና ቫይረስ የመመርመርያ ኪት ማምረቻ ፋብሪካ በይፋ መርቀው ከፈቱ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የማምረቻ ፋብሪካውን መርቀው የከፈቱት ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ነው፡፡
ቢ.ጂ.አይ ጤና ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለውጪ ሀገራት ገበያ የሚሆኑ የኮሮና ቫይረስ ፖሊመሬስ ቼይን ሪአክሽን (ፒ.ሲ.አር) መመርመሪያ ኪቶችን ማምረት ጀምሯል።
የመመርመሪያ ኪቱ ከቻይና መንግሥት ጋር በመተባበር የሚመረት መሆኑ ተነግሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጪ ሀገራት በሚደረገው ሽያጭ ለአፍሪካ ሀገራት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም፣ ፋብሪካው ቁጥራቸው በአጠቃላይ 3 ሚሊየን ለሚደርስ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እና በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለሚያልፉ መንገደኞች በክፍያ የላብራቶሪ አገልግሎት ይሰጣል።
ይህም የኢትዮጵያን እና የሌሎች አፍሪካ ሀገራትን የመመርመር አቅም ከፍ ያደርጋል።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከተገታ በኋላ፣ የማምረቻ ማዕከሉ የኤድስ ፣ የሳንባ ነቀርሳ እንዲሁም ሌሎች የሪል ታይም (አር.ቲ.) ፒ.ሲ.አር መመርመሪያ ኪቶችን ጨምሮ ሌሎች ኒዩክሊክ አሲድን መለያ ኬሚካሎችን ወደ ማምረት እንደሚሸጋገር ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የመመርመርያ ኪት ማምረቻ ፋብሪካ በይፋ መርቀው ከከፈቱ በኋላ የኮሮና ቫይረስ የፊልድ ሆስፒታል ግንባታ ያለበትን ደረጃ ጎብኝተዋል፡፡
ማዕከሉ ግንባታውን የጀመረው በግንቦት ወር ሲሆን በቅርቡ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ተቀብሎ ክህምና እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
በሰላማዊት ካሳ