በደቡብ ክልል ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ መንግስት ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል – አቶ ርስቱ ይርዳው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው በክልሉ በሚስተዋሉ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ መንግስት ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቁ፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ትልቅ ፈተና የሆነው በየቦታው የሚነሱ የህዝብን ጥያቄ ሽፋን በማድረግ የሚካሄዱ ህገ-ወጥነት ነው ሲሉ ነው የተናገሩት።
አቶ ርስቱ ህዝቡ በተለያየ መንገድ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ይኖሩታል፤ ይህንን ተከትሎ አንዳንድ ግለሰቦች እኔ ባለቤት ነኝና የህዝቡን ጥያቄ ልምራ የሚል መንፈስ በመያዝ ሲንቀሳቀሱ ይታያል ብለዋል።
እኔ ልምራ የሚለው አካል ሠላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ከዚህ ባፈነገጠ መልኩ የህዝቦችን ትስስር በሚበጥስና ወደ ግጭት በሚወስድ መንገድ ለማስኬድ እንደሚጥር አስታውቀዋል።
በዚህም የአደረጃጀት ጥያቄዎች በሰከነ አግባብ እልባት እንዳያገኝ የማደናቀፍ ሙከራዎች እንዳሉም አቶ ርስቱ ተናግረዋል።
የአደረጃጀት ጥያቄው ህገ መንግሥታዊ በመሆኑ 56ቱም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩል መብት እንዳላቸው አያጠያይቅም ብለዋል።
ሆኖም ሁሉም መክሮበት በሰከነ፣ በሰለጠነና ህዝቡን በተሻለ ዘላቂነት ጥቅሙን የሚያስከብርበት የአደረጃጀት ሥርዓት መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ለዚህ እውን መሆን ከመንግሥት አካላት በተጨማሪ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ የሃይሞኖት አባቶችና የባህል መሪዎች በተሳተፉበት መፈታት እንዳለበት ታምኖ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
በዚህ ሂደት ለውጡን ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ኃይሎችና አደናቃፊ ሚና የሚጫወቱ እንዳሉ ጠቅሰው፤ ለህዝብ ተቆርቋሪ መስለው ግጭትና ውጥረት ለመፍጠር እንደሚጥሩ አስታውቀዋል።
በዚህም መንግስት የጀመረውን ውይይት በሰከነ መንገድ ከሚፈታበት አውድ አውጥቶ በኃይልና ግጭት እንዲመራ ሲንቀሰቃሱ መስተዋሉን አስረድተዋል።
በቀጣይ በህገ ወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ገበቶ በተገኘ ማንኛውም አካል ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።
በመጨረሻም አቶ ርስቱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚሰጠው የውሳኔ ሀሳብ መሠረት የመጨረሻ እልባት እንደሚያገኝ መናገራቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።