በቂርቆስ ክ/ከተማ በአንድ ንግድ ቤት ውስጥ የተከማቸ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ተያዘ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በአንድ ንግድ ቤት ውስጥ የተከማቸ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ በህዝብ ጥቆማ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በቂርቆስ ክፍለከተማ ወረዳ 9 ደምበል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ የንግድ ቤት ውስጥ የተከማቸ ገንዘብ መኖሩን ከህዝብ ጥቆማ መምጣቱን የደምበል አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ሀላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን ደጀኔ ተናግረዋል።
ፖሊስም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማውጣት በንግድ ቤቱ ላይ ባደረገው ብርበራ ብሄራዊ ባንክ ካስቀመጠው መመሪያ ውጭ ተከማችቶ የተገኘ 2 ሚሊየን 631 ሺህ 735 አዲሱን እና ነባሩን የኢትዮጵያ ብር መያዙን ገልፀዋል፡፡
መንግስት እና የፀጥታ አካላት የሀገርን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት የሚያከናውኑትን በህገ- ወጦች ላይ እርምጃ የመውሰድ ተግባር በመደገፍ ህብረተሰቡ የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ኢንስፔክተር ሰለሞን ደጀኔ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ብሄራዊ ባንክ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ በእጅ ይዞ መንቀሳቀስ እና ማከማቸት መከልከሉ የሚታወስ ነው።