በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ሰብል እያወደመ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ እና ትግራይ ክልሎች የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገለፀ።
በምስራቅ አማራ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች የተከሰተው የአንበጣ መንጋው በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተነግሯል።
በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ የተከሰተው መንጋ የጉዳት መጠኑ ከፍተኛ መሆኑን የወረዳው አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡
በወረዳው የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ 24 ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት የወረረ መሆኑን የገለጸው የዞኑ ግብርና መምሪያ በበኩሉ ‘‘በወረዳው በ11 ቀበሌዎች ይገኝ የነበረ ሰብል ላይ ከ10 እስከ 100 በመቶ ጉዳት አድርሷል’’ ብሏል፡፡
አንበጣ መንጋውን ለመከላከል ሕዝቡን በማስተባበር እና አሮጌ የመኪና ጎማዎችን ከከተማ በማስመጣት ጭስ እያጨሱ በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብመድ ዘግቧል።
የመንጋው ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመምጣቱ የመከላከል ሥራው ውጤታማ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የአንበጣ መንጋው በትግራይ ክልል ደቡባዊ ትግራይ ዞን ሶስት ወረዳዎች ማለትም ራያ አዘቦ ፣ ራያ አላማጣ ፣ ራያ ጨርጨር ተከስቷል።
በዞኑ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ህብረተሰቡ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በዚህም ወጣቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች የፀጥታ አካላት፣ የተለያዩ የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ከፍሎች አንበጣውን የመከላከል ስራ እያከናወኑ ነው።