በአዲስ አበባ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በማጠር ለተለያዩ አገልግሎት ባዋሉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በማጠር ለተለያዩ አገልግሎት ባዋሉ አካላት ላይ ህጋዊ እርማጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ የመንገድ ልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ነገር ግን በከተማዋ የተለየዩ አካባቢዎች የሚገኙ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ ለማስተናገድ ከተነገቡበት አላማ ውጭ በማጠርና በመከለል ለግል ጥቅም የሚያውሉ ግለሰቦች በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ገልጿል ፡፡
በዋና ፣ መለስተኛ ፣ መጋቢና በውስጥ ለውስጥ መንገድ በአስፋልት፣ በኮብል ስቶንና በጠጠር የተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ቢሰሩም የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መንገዶችን በአጥር በመዝጋትና በር በመስራት ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ይህ ተግባር አብዛኛውን የመንገድ ተጠቃሚ ከማገልገል ይልቅ ለጥቂት የአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ለትራፊክ እንቅስቃሴ እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር የተደራሽነትና በእኩል ተጠቃሚነት መርህን የሚፃረር ተግባር ነው ሲል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስታውቋል ፡፡
እነዚህ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ለመጋቢ መንገዶች የትራፊክ እንቅስቃሴን በማስተንፈስ በኩል ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የተሰሩ በሮች እና አጥሮች በአስቸኳይ እንዲነሱ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ማሳሰቡን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት ክፍት ባላደረጉ አካላት ላይ ከሚመለከታቸው የደንብ ማስከበርና የፖሊስ አካላት ጋር በመተባበር አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወሰድ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ገልጿል፡፡