በጭፍራ ወረዳ ህገወጥ የጦር መሳሪያ በመደበቅ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተያዙ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 1፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፋር ክልል የጭፍራ ወረዳ ፖሊስ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ደብቀው አግኝቻቸዋለሁ ያላቸውን ሁለት ተጠርጠሪዎች መያዙን አስታወቀ።
የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር አብደላ ሁመድ ÷ግለሰቦቹ የተያዙት ትላንት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ነው ብለዋል።
በጭፍራ ከተማ ድንገት በተካሄደ የቤት ለቤት ፍተሻ ግለሰቦቹ ከደበቋቸው የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ጋር መያዛቸውን ተናግረዋል ።
በግለሰቦቹ መኖሪያ ቤቶች ተደብቀው ከተያዙ የጦር መሳሪያዎች መካከል አራት ክላሽንኮቨ ጠብመንጃና አራት ሽጉጦች እንደሚገኙበት ተናግረዋል ።
በተጨማሪም 2 ሺህ 289 የመትረየስና 112 የክላሽ ጥይቶች እንዲሁም 50 ባዶ የክላሽ ካርታና ሁለት የእጅ ቦምቦች መያዛቸውን ጠቅሰዋል ።
መሳሪያው የተገኘባቸው ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ገልጸዋል ።
የወረዳው ፖሊስ የጀመረውን ህገወጥ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።
ፖሊስ የህዝብና የሀገርን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ ህገወጥ እንቅስቃሴዎች ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት ህብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ዋና ኢንስፔክተር አብደላ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።