የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ለግብርና ምርታማነት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በተግባር እየታየ ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 1 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች በሰብል ልማትና ምርታማነት ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርሲ ዞን ለዓመታት በሴፍትኔት ፕሮግራም በተረጂነት የቆየችውን ዶዶታ ወረዳን ዛሬ ጎብኝተዋል።
በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ላይ በሰራነው ስራ በግብርና ምርታመነት ላይ ውጤት እያየን ነው ብለዋል።
ዶዶታ ወረዳን አምና መጎበኘታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወረዳው የተሰራው የአረንጓዴ አሻራ ስራ ለዘንድሮ የግብርና ሰብል ልማት አመች ሁኔታ መፍጠሩ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።
”በድርቅና በዝናብ እጥረት የሚታወቀው የዶዶታ መሬት በተከታታይ ዝናብ በማግኘቱ የተሻለና ተስፋ የሚሰጥ ስንዴ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ከማየት በላይ አሳማኝ ውጤት የለም” ብለዋል።
አርሶ አደሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአካባቢው ባከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ስራ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል ባለፉት ሁለት ዓመታት በችግኝ ተከላና እንክብካቤ ላይ ያሳየውን ተሳትፎ በመጪው ክረምትም መድገም እንደሚገባው አስገዝበዋል።
በመጪው የክረምት ወራት ከ6 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል አቅደናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በተመሳሳይ በጎሮቤት ሀገራት ከአንድ ቢሊየን በላይ ችግኝ በትብብር ለመትክል መታቀዱንም ገልጸዋል።
ይህም በረሃማነትን ከመቀነስ ባለፈ ሀገሪቷ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ በተከታታይ እንድታገኝ በማስቻል ለግብርና ልማትና እድገት በዘላቂነት አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ጭምር እንደሆነም ተናግረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በአራት ዓመት ከ20 ቢሊየን በላይ የተለያየ ዝርያ ያላቸውን ለምግብነትና ለደን ልማት የሚውሉ ችግኞቸን ለመትከል መታቀዱንም አመልክተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው÷ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ለክልሉ የሰብል ልማትና እድገት እያበረከተ ያለው አስታውጽኦ የላቀ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከናወነው ስራ በምርት እድገት ላይ አመርቂ ውጤት መታየቱን ጠቅሰው÷ በመጪው ክረምት በተቀናጀ መልኩ የአረንጓዴ አሻራ ስራን ለማከናወን ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በተገኘው ተፈጥሯዊ ምቹ ሁኔታ በመታገዝም በክልሉ በሴፍትኔት ፕሮግራም ስር የታቀፉ ወረዳዎች በምግብ ራሳቸውን ከመቻላቸውም ባለፈ በኩታ ገጠም ተደራጅተው ስንዴ፣ገብስ፣ጥራጥሬና የቅባት እህሎችን እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ የአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ ለዚህ ማሳያ መሆኗን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ÷በዝናብ እጥረት የሚጠቁ የምዕራብ አርሲ ዞን የሻሸመኔ፣ሻላና ሌሎች ወረዳዎችን በምሳሌነት መጥቅስ ይቻላል ብለዋል።
በዞኑ ዶዶታ ወረዳ ደሃ ደበሶ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ገመቹ ንጉሴ በበኩላቸው ÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ በአካባቢው የሰሩት ስራ ለሰብል ልማት ውጤማነት እገዛ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል።
አካባቢው ዝናብ አጠርና በድርቅ የሚጎዳ በመሆኑ ለረዥም ዓመታት ለተረጅነት ተዳርገን ነበር ያሉት አርሶ አደሩ ÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ያደረጉት ተሳትፎ አካባቢውን እንደለወጠው አስረድተዋል።
አምና የተሻለ ምርት አግኝተን ነበር ያሉት አርሶ አደሩ በዘንድሮ ዓመት የዝናብ ሁኔታ የተሻለ በመሆኑና በኩታ ገጠም ስንዴን በማልማታቸው ከሄክታር ከ50 እስከ 60 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የክልሉ ፕሬዘዳንት በየጊዜው መጥተው የእርሻ ስራችን ላይ የታየውን ለውጥ፣ያለብንን ችግርና ፍላጎታችንን ጠይቀው ድጋፍ በመስጠታቸው እናመሰግናለን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።