በአዲስ አበባ የሚገኙ የህወሃት አመራሮች በህወሃት የተደረገላቸውን ጥሪ እንደማይቀበሉ ገለጹ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የሚገኙ የቀድሞ የህወሃት አመራሮች ህወሃት በፌደራል መንግሥቱ የሚተላለፉ ህጎችን በመተላለፍ የህዝብ ሃላፊነት ይዘው በፌደራል መንግስት የስራ ሃላፊነት ላይ የሚገኙ አመራሮችን ለቃችሁ ኑ በሚል ያቀረበው ጥሪ አግባብ አለመሆኑን ገለጹ፡፡
አመራሮቹ ህወሃት የብልጽግና ፓርቲን ለመመስረት በሃዋሳ በተካሄደው ውይይት ላይ በሙሉ ተቀብሎ አሁን ላይ ያፈነገጠ አካሄድ መከተሉ የፖለቲካ ሸፍጥ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የህወሃት የአሁኑ አካሄድ ብልጽግና ፓርቲ በትግራይ ህዝብ ተቀባይነት እንዳይኖረው እና ህብረተሰቡ ሃሳቡን በነጻነት መግለጽ እንዳይችል የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ህወሃት የትግራይ ህዝብ እኩል ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ለማስመሰል የሚያደርገውን ተገቢ ያልሆነ አካሄድ ሊያስተካክል እንደሚገባ እና የትግራይ ህዝብም ይህን የተሳሳተ አካሄድ ሊረዳ እንደሚገባም አውስተዋል።
ብልጽግና የትግራይን ህዝብ ያገለለ ውሳኔ አንድም ቀን አሳልፎ አያውቅም የሚሉት የቀድሞ የህወሃት አመራሮች፥ ህወሃት ብልጽግና በትግራይ የሚሰራቸውን ስራዎች መካድ እና የትግራይ ህዝብ የተበዳይነት ስሜት እንዲኖረው የማድረግ ፍጹም የተዛባ ስራ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
በፌደራል ደረጃ የህዝብ ውክልና አግኝተው የተቀመጡ አመራሮችን አፈናቅሎ ለመውሰድ መሞከርም ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
የትግራይ ህዝብ ጥያቄ የኛም ጥያቄ ነው ያሉት የቀድሞ አመራሮቹ የትግራይ ህዝብ የህወሃትን የጥፋት እና የትርምስ አካሄድ ሊረዳው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
ነገሮችን ለማስተካከልም ሁለቱም ወገኖች ወደ ውይይት እንዲመጣ እንፈልጋለንም ብለዋል።
በይስማው አደራው