በኢትዮጵያ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚንቀሳቀስ አደረጃጀት እንዳይኖር የሚሰራ መሆኑን ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2013 ( ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚንቀሳቀስ አደረጃጀት እንዳይኖር ኀብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ ለማከናወን መወሰኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው 11ኛው የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ በዛሬው እለት ተጠናቋል።
ጉባኤው በአገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ፣ የፖሊስ ተቋማዊ የለውጥ ስራዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች የተዳሰሱበት ነበር።
ጉባኤውን አስመልክቶም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው ከውሳኔ የተደረሱ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የፖሊስ ሪፎርም ለማጠናከር በጉባኤው ላይ መወሰኑን ተናግረዋል።
ለሰራዊቱ ቴክኖሎጂ ማስፋፋት፣ ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት መፍጠር፣ የሰው ኃይል ግንባታ አጠናክሮ ማስቀጠል ውሳኔ ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑንም አንስተዋል።
የግጭት መነሻዎችን ማጥናት እና በጥናት የተደገፈ የቅድመ መከላከል ስራዎች ማካሄድ ሌላው የተወሰነበት ጉዳይ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
የኢ መደበኛ አደረጃጀትን ኀብረተሰቡን በማሳተፍ የማክሰም ስራ ለማከናወን ስምምነት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።
ታጣቂ ቡድኖችን ትጥቃቸውን በማስፈታት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ማድረግ ሌላው አጀንዳ መሆኑን ተናግረው ÷በዚህ አገር ላይ ሁለት ታጣቂ ኃይል መኖር አይችልም ብለዋል።
ኮሚሽነር ጀነራሉ ህብረተሰቡን ያማከለ የወንጀል መከላከል ስኬታማ እንዲሆን የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ማስፋትና ከህዝቡ ጋር ያለውን ቅንጅት ማሳለጥ በትኩረት ይሰራበታል ብለዋል።
የሰው ኃይል ማጥራትና ማብቃት የፖሊስን ተልዕኮ ለመወጣት እንደሚያስችል ጠቁመው ÷ ሰላምን በአስተማማኝ መንገድ ለመዘርጋት ለሰራዊት ጥራት ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
ከፌዴራልና ከክልል ፖሊስ ስምሪት ባሻገር ያልተሸፈኑ ቦታዎች ካሉም ሚሊሻዎችን በአግባቡ በማደራጀት የተናበበ ስራ በመስራት ችግሮችን መፍታት የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል።
ፖሊስ የሚመራበት ዶክትሪን በዚህ ዓመት ስልጠና መስጠት ይጀመራል ያሉት ኮሚሽነሩ ÷በፖሊስ ውስጥ ያለው ለውጥ እንዴት ይመራ? የሚለው ሌላው አጀንዳ መሆኑን አብራርተዋል።
ሞዴል ሰራዊት ማውጣት እንዲሁ የተጀመሩ ስራዎች እንደሚጠናከሩ ተገልጿል።
የሰራዊቱ ደሞዝ ስኬል ተጠንቶ መጠናቀቁን የገለጹት ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው የህክምና፣ የቀለብ፣ የሙያ አበል እንዲሁም የትምህርት እድል እንዲያገኙ ይሰራል ብለዋል።
የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ በአቋም መግለጫ መጠናቀቁን ኢዜአ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።