አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም ከደቡብ አፍሪካ የማምረቻው ዘርፍ ማህበር የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም ከደቡብ አፍሪካ ማምረቻው ዘርፍ ማህበር የስራ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
ማህበሩ በደቡብ አፍሪካ በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችን አባል አድርጎ የኢንዱስትሪ ዕድገትን፣ ስራ ፈጠራንና ሀገራዊ ዕድገትን ዋና ዓላማው አድርጎ የሚሰራ ተቋም ነው።
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያምም በትናንትናው እለት ከተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ ፊሊፕ ሮድሴት ጋር በጆሐንስበርግ ከተማ ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
በምክክር መድረኩ ላይ አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው፥ ኢትዮጵያ በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ተቋማት በኢትዮጵያ ያለው የተፈጥሮ ሃብት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሰው ኃይል፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ገበያ ዕድል፣ የኢቨስትመንት ፖሊሲዎች፣ ህጎችና ከመንግስት የሚደረጉ ዘርፈ ብዙ ማበረታቻዎች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡
የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ ፊሊፕ ሮድሴት፥ በተቋማቸው ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱና የደቡብ አፍሪካና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በውይይቱ መጨረሻ በማህበሩ የታቀፉት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት እንዲያደርጉ በኤምባሲውና በተቋሙ መካከል የጋራ ዕቅድ ተዘጋጅቶ እንደሚሰራና በፈረንጆቹ 2021 የአምራች ኢንዱስትሪ ተቋማት ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት እንዲያደርግ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
በተያያዘ የእርሻ ምርት ማቀነባበሪያ ማሽኖችን በማምረት ከተሰማራ ዴል አውቶሜሽን እና በዶሮ እርባታ ላይ ከተሰማራ ሴንቸሪያን ፖላሪቲ ከተባሉ ድርጅቶች ጋር ጋር ምክክር መደረጉንም ኤምባሲው አስታውቋል።
ሁለቱም ድርጅቶች በኢትዮጵያ ቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት እንዲያደርጉ ከስምምነት ላይ መደረሱም ተገልጿል፡፡