በአቶ ልደቱ አያሌው የክስ መቃወሚያ እና ዋስትና ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አቶ ልደቱ አያሌው በተከሰሱበት ሁለተኛው ህገመንግስቱን ለማፍረስ በማሰብ የሽግግር ሰነድ ማዘጋጀት ወንጀል ክስ ያቀረቡት ዋስትና ጥያቄ የተቀረጸው ድምጽ ግልባጭ ባለሙያ እረፍት በመውጣቱና ከመዝገብ ጋር ባለመያያዙ ምክንያት የክስ መቃወሚያውና ዋስትናው ላይ ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለህዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ፡፡
አቶ ልደቱ ከዚህ በፊት በተከሰሱበት ህገወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት ወንጀል የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት 100 ሺህ ብር ዋስ አስይዘው እንዲወጡ መፍቀዱን ተከትሎ ይግባኝ የቀረበለት ምስራቅ ምድብ ፍርድ ቤት ዋስትናውን ማጽናቱን ይታወሳል፡፡
ፖሊስም በዚህ 2ኛ ክስ በመመስረቱ አለመፍታቱን ገልጾ ነበር፡፡
አቶ ልደቱ ያሉበት የጤና ሁኔታ ህክምና ካላገኙ አስጊ መሆኑን የሚገልጽ የህክምና ማስረጃ ባሳለፍነው አርብ ለፍርድቤቱ በማቅረብ ከዚህ በፊት የተደረገላቸውን የልብ ቀዶ ጥገና የተገጠመላቸውን ሰው ሰራሽ መሳሪያ ተከትሎ የህክምና ቀጠሯቸው በማለፋ በድንገት ህይወታቸው አደጋ ላይ ሳይወድቅ በፊት ውጭ ወጥተው ታክመው ለመመለስ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ዐቃቤ ህግም በዋስ ቢወጡ በዛው ሊቀሩ ይችላሉ ሲል ዋስትናውን ተቃውሞ ተከራክሮ የነበረ ሲሆን የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድቤት ምስራቅ ምድብ ወንጀል ችሎትም ዋስትናው ላይ ለዛሬ ቀጠሮ የያዘ ቢሆንም በባለሙያው አለመኖር ምክንያት የዋስትና ጥያቄውም ሆነ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ክርክሩ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር ባለመያያዙ ለዋስትናውም ሆነ ለመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ብይን ለመስጠት ለህዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
በታሪክ አዱኛ