Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል የሲቪል ሰዎችን ደኅንነትና የሰብዓዊ እርዳታ አገልግሎት አቅርቦት ማረጋገጥ ያስፈልጋል- ኢሰመኮ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት እና የሰብዓዊ እርዳታ አገልግሎት አቅርቦት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ በፍጥነት እየተባባሰ የቆየውን  የትግራይ ክልል የፀጥታ ሁኔታ የሚያሳስበው መሆኑንና ክስተቱን በቅርበት እየተከታተለው እንደሚገኝ አስታውቋል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ፥ ለፌዴራል እና ለክልሉ የፀጥታ ኃይሎች የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት እና የሰብዓዊ መብቶችን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ እንዲጠብቁና እንዲያከብሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም፥ በተለይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ተፈጻሚ እንዲሆን የቀረበውን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ረቂቅ አዋጅ  መጽደቅ ላይ ለመምከር በሚሰበሰብበት በዛሬው እለት፣ ምግብና መድኃኒት የመሳሰሉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶችን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

እንዲሁም የግንኙነትና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ እንዳይቋረጥ ጥንቃቄ እንዲደረግ በማሳሰብ፥ የትግራይ ክልል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች እንደሚያስጠልልም አስታውሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.