መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ሃገርን የማዳን ጉዳይ እንጅ ከትግራይ ህዝብ ጋር እንደሚደረግ ጦርነት መመልከት አይገባም – አስተያየት ሰጭዎች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ወንጀለኛ የህወሓት አባላትን የመያዝና ሃገርን የማዳን ጉዳይ እንጅ ከትግራይ ህዝብ ጋር የሚደረግ ጦርነት አድርጎ መመልከት እንደማይገባ አስተያየት ሰጭዎች ተናገሩ፡፡
የተለያዩ ክልል ነዋሪዎች መንግስት በህወሓት ባለው ቡድን ውስጥ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በማውገዝ አስተያየታቸው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሰጥተዋል፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ በአማራ ክልል የባህር ዳር፣ ጎንደር እና ወልዲያ አካባቢ ነዋሪዎች ህወሓት የሀገር አለኝታ እና መከታ በሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመው ጥቃት በራሱ ወገን ላይ የተፈፀመ ትልቅ ክህደት ነው ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገር ዳር ድንበር ጠባቂና የወገን አለኝታ መሆኑን በመግለጽ ይህ አይነቱ ጥቃት ከዚህ በፊት ያልታየና በራስ ወገን ላይ የተፈጸመ የመጀመሪያው ክህደት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የህወሓትን አካሄድ ህገ ወጥ ነው ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢነት ያለው እና የሚደገፍ መሆኑንም ገልጸዋል፤ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸሙ ለነበሩና ለተፈጸሙ ጥቃቶች መነሻቸው ህወሓት እንደነበር በመጥቀስ፡፡
ህዝቡም ከዚህ ቀደም በህወሓት ላይ እርምጃ ይወሰድ ዘንድ ሲጠይቅ እንደነበር በማስታወስም እርምጃው ቢዘገይም ሃገርና ህዝብን ከማዳን አንጻር ተገቢነት ያለውና አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የክልሉ ወጣቶችም መከላከያው በተሰማራባቸው አካባቢዎች ከደም ልገሳ ጀምሮ ማንኛውንም ድጋፍ በማድረግ ለስኬታማነቱ አጋርነታቸውን እያሳዩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ አንጻርም በተለይም የትግራይ ክልል ወጣቶች በመከላከያ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ ከሃገር መከላከያ ሰራዊት ጎን እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተያያዘም በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እና አካባቢዋ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች፥ በህወሓት ውስጥ ያለው ፅንፈኛ ቡድን በሰሜን እዝ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት አውግዘዋል።
መንግሰት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት የፈፀመውን የጥፋት ቡድን ተከትሎ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉም ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በዴሌ ዞን የበደሌ ወረዳ ነዋሪ የህብረተሰብ ክፍሎችም ባለፉት 27 ዓመታት በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ ሲፈፅም የነበረው የህወሓት ቡድን ሀገሩን እና ህዝቡን ለመጠበቅ ቀን ከሌት የሚቆመው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመው ተግባር ለሀገሪቱ ያለውን ጠላትነት ያሳየበት መሆኑን አውስተዋል፡፡
መንግስትም በዚህ የጥፋት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ መሆኑንም አስተያየታቸውን የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎቹ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በጅማ ዞን የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችም መንግስት በህወሓት ውስጥ ያለ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
በጅማ ዞን ሰቃ ጮቆርሳ የሚገኙ አርሶ አደሮችም መንግስት በጽንፈኛ የህወሓት ቡድን ላይ የሚወስደውን እርምጃ እንደሚደግፉ በመጥቀስ፤ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ነዋሪዎችም መንግስት በጽንፈኛው ህወሓት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ህጋዊ፣ ፍትሃዊና ትክክለኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጭዎቹ መንግስት በጽንፈኛው ህወሓት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ህጋዊ፣ ፍትሓዊና ትክክለኛ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ነው ያሉት።
የትግራይ ክልል ህዝቦችም መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ የትግራይ ህዝብ ጠላት ከሆነው ከአሸባሪው ህወሓት ቡድን ጋር መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ፥ የዴሞክራሲ ፈላጊ የክልሉ ተወላጆችም እጅ ለእጅ ተያይዘው ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ ቡድኑን ከራሳቸው ሊያስወግዱ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አስተያየት ሰጭዎቹ መንግስትም እየወሰደ ባለው እርምጃ ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱ ከለላና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም ነው የጠየቁት፡፡