ባለስልጣኑ በጥቃቅን እና አነስተኛ ለተደራጁ ማህበራት የስራ ዕድል ሊፈጥር ነው
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን በጥቃቅን እና አነስተኛ ለተደራጁ ማህበራት የስራ ዕድል ሊፈጥር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ የስራ ዕድል ፈጠራውን ከከተማ አስተዳደሩ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ እና ከወጣቶችና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ጋር በመቀናጀት እያከናወነ መሆኑ ታውቋል፡፡
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ከ781 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን በጀት በጥቃቅን እና አነስተኛ ለተደራጁና 169 አዲስ እና ነባር ማህበራት ውስጥ ለሚገኙ ከ1 ሺህ 700 በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መዘጋጀቱን ነው የገለፀው፡፡
ለስራ አጥ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር በከተማ ደረጃ ለተያዘው የድህነት ቅነሳ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት ከነባር ማህበራት በተጨማሪ በተያዘው በጀት ዓመት ከ64 በላይ ለሚሆኑ አዲስ ማህበራት የስራ ትስስር ለመፍጠር የቅድመ ዝግጅት ስራ ማጠናቀቁን የሶስተኛ ወገን ስራ ዕድል ፈጠራና መረጃ ማዕከል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዋሲሁን ዘውዴ ገልፀዋል፡፡
የውሃ እና ፍሳሽ ማንሆል ማምረት፣ የፍሳሽ መስመር ዝርጋታ እና ቅጥያ፣ ያልተጠናቀቁ መፀዳጃ ቤቶች ፣ አጥር ፣ የጥበቃ ቤት፣ ግምጃ ቤት እና የጄኔሬተር ቤት ግንባታ የስራ እድል የሚፈጠርባቸው የስራ ዘርፎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
በተጨማሪም ከ100 በላይ ለሚሆኑ አዲስ የቆጣሪ አንባቢ ማህበራት እና ከ384 በላይ ለሆኑ የቁፋሮ ማህበራት የስራ ትስስር እንደሚፈጠር አቶ ዋሲሁን መግለፃቸውን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡