የአፍሪካ ወደቦች ፎረም በጅቡቲ ተካሄደ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ወደቦች ፎረም በጅቡቲ ተካሄደ፡፡
ፎረሙ በሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነትና ትብብርን በማጠናከር በኮቪድ 19 ወቅት የነበረው የሀገራት ኢኮኖሚና የንግድ መቀዛቀዝ ማጠናከርን ያለመ መሆኑ ታውቋል፡፡
በመድረኩ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አወል ወግሪስ መሰል ፎረሞች መካሄዳቸው በ2063 የተቀመጡ አጀንዳዎችን ለማሳካትና ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ የአፍሪካን አንድነት የበለጠ ለማጠናከር ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስቴር የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር መግባቱን ያነሱት ሚኒስትር ዲኤታው ደረቅ ወደቦችንና መሰረተ ልማቶችን በመስፋፋት ረገድ ሃገራዊ ግንኙነቶች በሚያጠናክርበት መልኩ መታቀዳቸውን አብራርተዋል።
በተለይም የጅቡቲ ወደቦች ዋነኛ የገቢና ወጪ ንግድ የሚከናወንበት በመሆኑ በሁለቱ ሃገራት ያለው የመሰረት ልማት ማስፋፋት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለወደብ ተጠቃሚው ማህበረሰብ ሁሉ በመስጠት የሎጅስቲክስ ጊዜና ወጪ እንዲቀንስ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሠራ መግለፃቸውን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በጉባኤው ላይ ከ100 በላይ ሃገራት ተወካዮች በአካል ከ200 በላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ደግሞ በቪዲዮ ኮንፈረንስ መድረኩን መሳተፋቸው ታውቋል፡፡