ባለስልጣኑ በአራት ወራት ውስጥ 245 ኪሎ ሜትር ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ስራዎች አከናወነ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በአራት ወራት ውስጥ 245 ኪሎ ሜትር ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ስራዎችን ማከናወኑን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ ለትራፊክ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ የሆኑ ዋና ዋና፣ የቀለበት መንገድ እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ እና አቋራጭ መንገዶችን የጉዳት መጠናቸውን በመለየት የጥገና ስራዎችን በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ነው የገለፀው።
በዚህም በአራት ወራት ውስጥ 13 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ 220 ኪሎ ሜትር የድሬኔጅ መስመሮች ጽዳትና ጥገና፣ 9 ኪሎ ሜትር ጠጠር (አክሰስ) መንገድ፣ 3 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድና ከርቭ ስቶን የጥገና ስራዎች ተከናውኗል ነው ያለው ባለስልጣኑ፡፡
በተጨማሪም በዘርፈ ብዙ የመንገድ ጥገና ስራዎች ውስጥ በቁጥር 889 የተበላሹ የመንገድ መብራቶች ጥገና የተደረገላቸው ሲሆን 220 አምፖሎች በአዲስ የመየቀር ስራ እንዲሁም ድልድይና የድጋፍ ግንብ፣ የእግረኛ መከላከያ አጥር የጥገና ስራዎችም ተከናውነዋል ተብሏል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ2013 በጀት ዓመት ከ525 ኪሎ ሜትር በላይ በተለያዩ ምክንያቶች ለብልሽት የተዳረጉ የአስፋልትና ሌሎች መንገድ የጥገና ስራዎችን ለማከናወን በዕቅድ የያዘ ሲሆን ይህም የከተማዋን መንገዶች ለእንቅስቃሴ ምቹ እና የትራፊክ ፍሰቱ የተሳለጠ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።