አርሲ ዩኒቨርሲቲ 60 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አርሲ ዩኒቨርሲቲ 60 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ፡፡
ዩኒቨርሲቲው 60 የህክምና ዶክተሮችን ጨምሮ በኮቪድ ምክንያት በስነ ስርዓቱ ላይ መታደም ያልቻሉ 1 ሺህ 64 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዱጉማ አዱኛ ስለሰው ልጆች ጤና በሚገደው የህክምና ሙያ የተመረቁ ባለሙያዎች ለሀገርና ወገናቸው በርትተው እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተ ገና አምስት አመታትን ቢያስቆጥርም ከእድሜው በላይ እየሰራ ነው ተብሏል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ የኢትዮጵያ ንጋት በቀረበበት ጊዜ የተመረቁ መሆናቸውን በመጥቀስ አጋጣሚውን እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የጤናው ዘርፍ ሰብዓዊ ርህራሄንና የሙያ ስነምግባርን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡
ተመራቂዎቹም የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በአፈወርቅ እያዩ