በጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የተመራ ቡድን የደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች የህክምና ማዕከላትን ጎበኘ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የተመራና የተለያዩ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ ቡድን በበአማራ ክልል ደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች በመገኘት የህክምና ማዕከላትን ጎበኘ።
በዶክተር ደረጀ ዱጉማ የተመራው የስራ ኃላፊዎች ቡድን ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ፣ ከመከላከያ ጤና መምሪያ እና አማራ ክልል ጤና ቢሮ የተውጣጣ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ቡድኑ በደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ መርሳ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ ቆቦ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ ወልዲያ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ሌሎች የህክምና ማዕከላትን ተዘዋውሮ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱም መደበኛው የጤና አገልግሎት እና በህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሰማሩ የፀጥታ አካላት እየተሰጠ ያለው የጤና አገልግሎትን ተመልክተዋል።
የጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በዚሁ ወቅት፥ ከአዲስ አበባ እና ከተለያዩ አከባቢዎች የተላኩ የጤና ባለሙያዎች በጤና ተቋማት ካሉ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት እየሰጡ ያሉት አገልግሎት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ከመከላከያ ጤና መምሪያ የተገኙ የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው የጤና ባለሙያዎች እየሰጡ ላሉት ሙያዊ አገልግሎት ትልቅ ክብር ይገባቸዋል ብሏል።
በሁሉም ጤና ተቋማት የጤና ባለሙያዎች እጥረት እንደሌለ ማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን፥ የአከባቢው ህብረተሰብ ከጤና ባለሙያዎችና ታካሚዋች ጎን በመቆም አስፈላጊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑም ተገልጿል።
በሁሉም ተቋማት ላይ መሰረታዊ የሆኑ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች የተሟሉ ሲሆን፥ በተወሰኑ ተቋማት የሚያስፈልጉ ተጨማሪ የኦርቶፔድክስና ለድንገተኛ አደጋ ህክምና አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶች በአጭር ጊዜ ከማዕከል እንደሚላኩም አስታውቅዋል።
በተያያዘ ቡድኑ የኮምቦልቻ አጠቃላይ ሆስፒታል ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ የተመለከተ ሲሆን፥ የሆስፒታሉ ግንባታ ከተጀመረ ረጅም ጊዜ ቢሆንም አሁን ላይ ግንባታው በጥሩ ሁኔታ እየተጠናቀቀ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ደረጀ ገልፀዋል።
ሁሉም የሚመለከተው አካላት ትኩረት ስጥተው የተቀሩ ስራዎች በአጭር ጊዜ አልቆ ሆስፕታሉ ስራ መጀመር እንዳለበት አሳስበዋል።