Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 2 ዓመታት ተግባራዊ በተደረጉ የለውጥ ስራዎች የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ መሻሻሉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ባለፉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ ባደረጋቸው የለውጥ ሥራዎች የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ የተሻሻለ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀን “ለሰብዓዊ መብቶች መከበር እንትጋ” በሚል መሪ ሃሳብ በቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

የፌደራል ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ተስፋዬ ዳባ በእዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአሰራር ለውጥ ካደረጉ ተቋማት መካከል የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

ለ27 ዓመታት የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፀምባቸው ከነበሩ ተቋማት መካከልም አንዱ ማረሚያ ቤቶች እንደነበር አስታውሰው፣ ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ ባደረጋቸው የለውጥ ሥራዎች በታራሚዎች አያያዝ ላይ ይስተዋል የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሏል ብለዋል።

“ኮሚሽኑ አሁን እያሳየ ያለውን በጎ ተግባር በማስቀጠል በኢትዮጵያ ለተጀመረው የዴሞክራሲና የብልጽግና ጉዞ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል” ብለዋል።

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የለውጥ ሥራ አመራር ዳይክቶሬት ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ወንድሙ፥ ኮሚሽኑ በዘረጋው የለውጥ ሥራ አመራር የህግ ታራሚዎችን ሰብዓዊ መብቶች የሚጥሱ አሰራሮችና ተግባራት ተወግደዋል ብለዋል።

ቀደም ሲል የህግ ታራሚዎችን በጨለማ ቤቶች ማቆየት፣ የምግብ አቅርቦት እጥረት እንዲሁም በታራሚዎች ላይ የሚፈጸሙ የድብደባና መሰል የኃይል እርምጃዎች አለመኖራቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተወካይ አቶ ምስጋናው ኤርሚያስ በበኩላቸው፥ ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ሥራዎች ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ገልጸዋል።

“ማረሚያ ቤቶች ስማቸው መነሳት ያለበት በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሳይሆን ታራሚን በአግባቡ አርሞና አምራች ኃይል አድርጎ ወደ ህብረተሰቡ በመቀላቀል ነው” ያሉት ደግሞ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል አባሶ ናቸው።

ለዚህም የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ በአሁኑ ወቅት አራት የኢንዱስትሪ ማዕከላትን በመገንባት ታራሚውን አምራች ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀን በከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት ሲከበር የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን የታራሚዎች የሥራ ውጤቶችም መጎብኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.