በመዲናዋ በ831 ሚሊየን ብር ዘመናዊ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ሊገነባ ነው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ በ831 ሚሊየን ብር ወጪ ዘመናዊ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ህንጻ ግንባታ ለማካሄድ ከቻይናው የኮሙዩኒኬሽን እና ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲ ሲ ሲ ሲ) ጋር ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ እና በቻይናው የኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ መካከል በዛሬው እለት መፈረሙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ማዕከሉ የትራፊክ መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የትራፊክ መብራቶችን የቆይታ ጊዜ እንደ ትራፊክ ፍሰቱ መጠን የመቀያይርና ልዩ ልዩ የትራፊክ ፍሰት ማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የማድረግ ስራም ይከናወንበታል ተብሏል።
በተጨማሪም አሽከርካሪዎች የመንገዶችን የትራፊክ ሁኔታ ቀድመው እንዲያውቁና አማራጭ መንገዶችን እንዲፈልጉ መረጃ የመስጠት፣ የትራፊክ ህጎችን የሚተላለፉ አሽከርካሪዎችን የመለየት እንዲሁም የትራፊክ ፍሰት፣ የአደጋ እና የደህንነት መረጃዎች ወደሚመለከታቸው ልዩ ልዩ ተቋማት በጊዜው እንዲተላለፉ ማድረግ ያስችላል ነው የተባለው።
ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሲበቃ በከተማዋ የሚታየውን የትራፊክ ፍሰት ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።
የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከሉ ከመሬት በታች አራት ወለሎች ሲኖሩት፥ ከትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል በተጨማሪ መረጃ ማደራጃ ክፍሎች፣ የወንጀልና የአደጋ መከላከያ መረጃ ቢሮዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ያካትታል።
ማዕከሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ዘመኑ ያፈራቸው ቴክኖሎጂዎች እና መሰረተ ልማቶች የሚሟሉለት ሲሆን በ18 ወራት ውስጥ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግ በፊርማ ስነ-ስርአቱ ላይ ተጠቅሷል።