Fana: At a Speed of Life!

የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት ለህወሓት የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር ማረጋገጡን ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 15 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ ለህወሓት የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር ፖሊስ በምርመራ ማረጋገቱጡን ገለጸ።
ፖሊስ እነሙሉጌታ ተስፋ ኪሮስን ጨምሮ ሶሰት ተጠርጣሪዎች ላይ ከዚህ በፊት በተሰጠው 10 ተጨማሪ ቀናት የሰራውን የምርመራ ስራ ለችሎቱ አብራርቷል።
ዛሬ በችሎት የቀረቡ ተጠርጣሪዎች ሃይላይ መዝገቡ፣ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ እና ሳሙኤል አባዲ ሲሆኑ÷ በዚሁ መዝገብ ተካቶ ከዚህ በፊት በችሎት ቀርቦ የነበረው ሃየሎም ዘራብሩክ በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ ቁጥር 28 መሰረት በዋስ መፈታቱን ፖሊስ ለችሎቱ አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በተጠረጠሩበት ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ ሙከራ ወንጀል ፖሊስ በተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ በሰራው የምርመራ ስራ የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ ለህወሓት የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን በተመለከተ መረጃ አግኝቻለሁ ሲል ገልጿል።
በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለህወሓት ቡድን ማጠናከሪያ ሪፎርም በሚል ሽፋን አባላትን ሲያደራጁ እንደነበር መረጃ ማግኘቱንም ፖሊስ አስታውቋል።
ከተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤትም በርካታ የገንዘብ መጠን ያላቸው በተለያዩ የባንክ ደብተሮች ሂሳብ ተጠቅመው ለተፈጸመው ወንጀል በገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር የሚያሳይ በሰንጠረዥ የተካተተ የስም ዝርዝር መረጃ ማግኘቱንም አብራርቷል።
በአዲስ አበባ ልዩ ዞን የህወሓት ፅህፈት ቤት ለመመስረት በሚል ሽፋን ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት ሲያደርጉ እንደነበርም በመረጃ ማረጋጋጡን ገልጿል።
ፖሊስ በዚህ መልኩ የሰራቸውን በርካታ የመርመራ ስራዎች ገልጾ ÷ ለተጨማሪ የሰው ምስክር ቃል ለመቀበልና ሌሎች ምርመራዎቸን ለማከናወን ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል ሲል 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ተጠርጣሪዎቹ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው በመግለጽ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ እንደማይገባ ተቃውመው ተከራክረዋል።
የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ጠበቆቸም በፖሊስ እየተገለጸ ያለው ምርመራ ተገቢነት የሌለው ነው እርሳቸው ነጋዴ ናቸው በስራቸው እንቅስቃሴ የነበረ ገንዘብ ነው በሚል ተቃውመው ተከራክረዋል።
መርማሪ ፖሊሰም ተቋማችን ህጋዊ ተቋም ነው እኛ ሃሰተኛ መረጃ አይደለም የምንሰበብው ወንጀሉ የተፈጸመው ከአዲስ አበባ ውጭ እንጅ በአዲስ አበባ አይደለም የተባለው አግባብነት የሌለው ነው፤ ለተፈጸመው ግድያ እና ንብረት ጉዳት በገንዘብ ሲደግፉ ነበር ነው ያልኩት ብሏል።
ከዚህ ባለፈም በወንጀሉ የሞተው ሰው ነው በሞቱ ዜጎች ላይ ለመሳለቅ ነው እንጂ ወንጀሉ በሃገር ላይ የተፈጸመው ወንጀል የሚታወቅ ነው ሲል የጠበቆቻቸው ክርክር ላይ የሙያ ስነምግባር ይጠበቅ ሲል ፍርድቤቱ እንዲመዘግብለት ጠይቋል።
ጠበቃውም እኛን ለማሳቀቅ ነው በማለት፤ እንዴት በሞቱ ሰዎች እንቀልዳለን ሙያቸንን ነው የምናስቀድመው ይህ የችሎቱን አመራር የሚረብሽ ነው ሲሉ ለፖሊስ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ችሎቱም መዝገቡን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት በይደር ለነገ ቀጠሮ ይዟል።
በታሪክ አዱኛ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.