ኢሰመኮ በኮንሶ ዞን አካባቢ ባገረሸ ግጭት መነሻነት ከኅዳር 1 እስከ ኅዳር 11 ቀን ድረስ 66 ሰዎች መገደላቸውን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኮንሶ ዞን አካባቢ ባገረሸ ግጭት መነሻነት ከኅዳር 1 እስከ ኅዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 66 ሰዎች መገደላቸውን የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮን ጠቅሶ አስታወቀ፡፡
ለዓመታት የተገነቡ ቀበሌዎችም በስድስት ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ አመድነት መቀየራቸውን ነው ባወጣው ሪፖርት የገለጸው፡፡
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ 39 ሰዎች መቁሰላቸውን እንዲሁም 132 ሺህ 142 ሰዎች መፈናቀላቸውን ጠቅሷል፡፡
ከኅዳር 12 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ኅዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ወደ አካባቢው የክትትል ቡድን ልኮ ምርምራ ማድረጉን የገለጸው ኮሚሽኑ የክትትል ቡድኑ በሀይበና እና በአይዴ ቀበሌዎች እንዲሁም በአርባምንጭ፣ በጊዶሌ እና በካራት ከተሞች በመገኘት ተጎጂዎችንና ቤተሰቦቻቸውን፣ የዓይን ምስክሮችንና የተለያዩ የመንግስት አካላትን ማነጋገሩን ነው የጠቀሰው፡፡
በርካታ ሰዎች በጥቃት ፈጻሚዎች በጭካኔ እና በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ እንዲሁም በርካታ ቀበሌዎች ውስጥ መኖሪያ ቤቶች፣ የተሰበሰበን እህል ጨምሮ ንብረት እና የእርሻ ቦታዎች መሉ በሙሉ እና በከፊል በእሳት መውደማቸውን ነው ያስረዳው።
ከጥቃቱ መሸሽ ያልቻሉ አቅመ ደካማ ሰዎች ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ተቃጥለው ለህልፈት መዳረጋቸውን ጠቅሶ ግጭቱ መጠነ ሰፊ የሆነ ሰብአዊ ቀውስ አስከትሏልም ነው ያለው፡፡
የችግሩ መሰረታዊ ምክንያት ወይም የስር መንስዔ ገና እልባት ያላገኘና ግጭቱ መልሶ ሊያገረሽ የሚችል በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ የመፈለጉ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአሁኑ ወቅት በግጭቱ ለተፈናቀሉና በተለያዩ አካባቢዎች ተጠልለው ለሚገኙ ሰዎች አስፈላጊውን ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ቀዳሚው ስራ መሆኑን ኮሚሽኑ ጠቅሷል።
የመንግስትን መዋቅር ይዘው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ግጭቱን የሚያነሳሱ፣ የሚደግፉና የሚያባብሱ ወይም ግጭቱን ባለመከላከል ኃላፊነታቸውን በማይወጡ ሰዎች ላይ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ የእርምት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።
በአካባቢው እየተስፋፋ እንደመጣ የሚነገረው የሕገወጥ መሳሪያ ዝውውር ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር ማጠናከርም በኮንሶ ዞንና በአካባቢው በየጊዜው የሚያገረሹ ግጭቶችን ለማስቀረት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑንም በሪፖርቱ አንስቷል።
ጥቃቱ የደረሰው ኮንሶ ዞን አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከጥቅምት 21 ቀን ጀምሮ አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ መሆኑንም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!