ተጓዳኝ ህመም የሌለባቸውና በዕድሜ ወጣት የሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው እያለፈ ነው-ዶክተር ውለታው ጫኔ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 18 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ተጓዳኝ ሕመም የሌለባቸውና በዕድሜ ወጣት የሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን በሚሊኒየም የኮቪድ 19 ሕክምና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ውለታው ጫኔ አስታወቁ።
ቫይረሱ በራሱ ተጨማሪ ተጓዳኝ የጤና ችግሮችን እንደሚያስከትል አሳሰቡ።
ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ውለታው ጫኔ የኮቪድ 19 ቫይረስ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸውንና በዕድሜ የገፉትን ብቻ ነው የሚያጠቃው የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ አሁንም በስፋት ይስተዋላል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የታየው ግን የተጠቁት ተጓዳኝ ህመም የሌለባቸው በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ጭምር ናቸው።
ምንም ዓይነት ተጓዳኝ ህመም የሌለባቸውና በዕድሜ ወጣት የሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተሩ፣ ምናልባት በዕድሜ የገፉና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ላይ የበለጠ ቢከፋም እየሞቱ ያሉት ግን በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ዜጎች ናቸው ብለዋል።
አሁን ላይ ባለው ሁኔታ የጽኑ ህሙማን ታካሚዎች እና በኮቪድ 19 ሕይወታቸው የሚያልፍ ወገኖችም ቁጥር ጨምሯል ነው ያሉት።
የማሽን ድጋፍ እና ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ መምጣቱን አስታውቀዋል።
ዶክተር ውለታው አያይዘውም ከወራት በፊት 60 በመቶ የሚሆኑ ታካሚዎች ቶሎ አገግመው የሚወጡ ታካሚዎች የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ግን ከ50 በመቶ በላይ ያለው ታካሚ በፀና ታሞ የሚመጣ ነው።
ይህም የሚያሳየው መዘናጋት መኖሩንና ከውጭ ተጎድተው መቆየታቸውን ነው።
ጥንቃቄ በጎደለ ቁጥር የቫይረሱ ዝውውር እየሰፋ እንደሚሄድ ያመለከቱት ዶክተሩ ከሰዎች ጋር ሳይገናኙ በቤት ውስጥ የቆዩ እናቶችና አባቶች መዘናጋት በመኖሩ ምክንያት በቫይረሱ የመጠቃት ዕድላቸው እየጨመረ መጥቷልም ነው ያሉት።
ይህም የሞት ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!