Fana: At a Speed of Life!

በህንድ  የኢትዮጵያ  ኤምባሲ የኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝም ማስዋወቂያ መድረክ አካሂደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በህንድ ኒውዴልሂ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የህንድ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ጋር በመተባበር የኢፌዴሪ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በተገኙበት ከ130 በላይ የህንድ ኩባንያዎች የተሳተፉበት የቨርችዋል የማስተዋወቂያ መድረክ ተካሄደ።

በመድረኩ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ፣ በህንድ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ትዝታ ሙሉጌታ፣ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግን ጨምሮ የቱሪዝም ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲሁም የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የስራ ኃላፊዎች  ተገኝተው ገለፃ አድርገዋል፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በመድረኩ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር  ኢትዮጵያና ህንድ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ታሪካዊ ትስስር ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን ገልጸው፤ የውጭ ንግድንና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ ኢኮኖሚያዊ ሪፎርሞችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የውጭ ንግድ ለማሳደግ፣ የሚያጋጥሙ የንግድ ማነቆዎችን ለመቀነስ እና መልካም የንግድ ግንኙነት ለመገንባት የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ በመግለጽ፤ በኢትዮጵያ ካለው ምቹ የኢንቨስትመንት እድል አንፃር የህንድ ባለሃብቶች ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

አምባሳደር ዶክተር ትዝታ ሙሉጌታ እንዳሉት በኢትዮጵያ ያለው የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስርዓት፣ የተማረና አምራች የሰው ሃይል፣ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ ሰፊ ገበያ  መኖሩን ገልጸዋል።

በተጨማሪም መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረትና የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን በመጠቀም የህንድ ባለሃብቶች በሀገሪቱ ኢንቨስት ቢያደርጉ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ወደ ህንድ የሚገቡ ምርቶችን በጥራትና በመጠን ለመጨመር በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የገለፁት አምባሳደሯ፤ የህንድ ባላሃብቶች ካላቸው የቴክኖሎጂና ከፍተኛ ልምድ አንጻር እሴት በሚጨምሩ ዘርፎች፣ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ በማኑፋክቸሪንግና በቱሪዝም ዘርፎች መዋለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱም  ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በነበራቸው አጭር ቆይታ መንግስት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን እንደተገነዘቡ ገልፀው፤ የህንድ ባለሃብቶች ሊሳተፉ የሚችሉባቸው ብዙ ዘርፎች መኖራቸውንም ነው ያስታወቁት።

በኢትዮጵያ  ኢንቨስት ያደረጉ ሶስት የህንድ ኩባንያዎች ልምዳቸውን ለተሳታፊዎች ያካፈሉ ሲሆን፤ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.