Fana: At a Speed of Life!

የሕዝቦችን አንድነት የሸረሸረውን የህወሃት የተሳሳተ ትርክት ለማጽዳት እየተሰራ ነው – የክልል ምክር ቤቶች

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያዊያንን አንድነት የሸረሸረውን የህወሃት የሃሰት ትርክት ከመሰረቱ ለማስወገድ እየተሰራ መሆኑን የክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች ገለፁ።

የአማራ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝና የደቡብ ክልሎች ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎችና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደገለጹት በየአካባቢያቸው የሕዝቦችን አንድነትና ትስስር የሚያጠናክሩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ “በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የሚፈፀም ግድያ፣ ማፈናቀልና ንብረት ማውደም የኢትዮጵያዊያን መገለጫዎች አይደሉም” ብለዋል።

እነዚህ ተግባራት የህወሃት አመራሮች የሴራ ፖለቲካ ስልት የሆነው ሕዝብን በመከፋፈል የግል ጥቅም ማሟያዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በጋራ ከማልማት ይልቅ እርስ በርስ በመጋጨት ለልማት፣ ለሠላምና ለአንድነት ትኩረት እንዳይሰጡ ሲሰራ እንደነበር አስታውሰዋል።

“የሕዝቦች ጠላት የሆነው ህወሃት በትብብር ይደምሰስ እንጂ ፍርስራሾቹ ኦነግ ሸኔና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በመኖራቸው እነዚህን ከመሰረቱ ለማፅዳት አሁንም ትኩረት ያሻል” ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታደለ ተረፈ በበኩላቸው ባለፉት 28 ዓመታት አገራዊ አንድነት እንዲቀጭጭና የብሔር ማንነት ጎልቶ እንዲወጣ መሰራቱ ትልቅ ችግር መሆኑን አውስተዋል።

“በዚህም ዜጎች ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለዋል፣ ተገድለዋል ለዘመናት ያፈሩትን ንብረትም አጥተዋል” ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት ክልሉ ከሚያዋስናቸው አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ጋር የቀደመ አብሮነቱን ለመመለስ ልማትና ማኅበራዊ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ታደለ የብሔር ማንነትና አገራዊ አንድነት ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ጠንካራ ስራ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

“በደቡብ ክልል የሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከርና መቻቻልን ለማጎልበት እየተሰራ ነው” ያሉት በክልሉ ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ቀለምወርቅ ለገሰ፤ የሚከሰቱ ችግሮችን ከመሰረታቸው ለመፍታት እየተሰራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.