በ901 ሺህ 814 ዩሮ 19 አዳዲስ የወደብ ማሽነሪዎችን ግዥ ተፈጸመ
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ለሞጆ ወደብና ተርሚናል 19 አዳዲስ የወደብ ማሽነሪዎች ግዥ መፈፀሙን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ካሉት 9 ወደብና ተርሚናሎች የሎጅስቲክስ ስራውን በማሳለጥ ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው የሞጆ ወደብና ተርሚናልን አገልግሎት ለማዘመን እና ያለውን የማሽነሪ አቅም ለማሳደግ ግዥ መፈፀሙን ነው ያስታወቀው።
ማፊ ትራንስፖርት ሲስተም ከተባለ የጀርመን ኩባንያ በ901 ሺህ 814 ዩሮ ስምንት የተርሚናል ትራክተር እና 11 ተርሚናል ቻሲስ መግዛቱ ተጠቁሟል፡፡
ማሽነሪዎቹ በተለየ መልኩ ከባቡር ላይ እና ተርሚናል ውስጥ ኮንቴነር በማንቀሳቀስ አገልግሎታቸው የጎላ ሲሆን ከባቡር ወደ ተርሚናል ያለውን የኮንቴነር ምልልስ በማፋጠን የባቡሩን ኦፕሬሽን ከማቀላጠፋቸው ባሻገር ኮንቴነሮችን ከተርሚናል ወደ ፍተሻ ስፍራ በተፈለገው ፍጥነት ለማጓጓዝ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ የወደብ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
የማሽነሪዎቹ የግዥ ስምምነት የመለዋወጫ ዕቃዎችን እና የባለሙያ ስልጠናን ያካተተ በመሆኑ ማሽነሪዎቹን ለሚያንቀሳቅሱ ባለሙያዎች ተገቢው የደህንነት እና የማሽን አያያዝ ስልጠና በመስጠት ማሽነሪዎቹን ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅቱ ተጠናቋል ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተገዙ 48 የተለያዩ የወደብ ማሽነሪዎችን ገጣጥሞ ለአገልግሎት ማዘጋጀቱን ነው ድርጅቱ የገለፀው፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!