Fana: At a Speed of Life!

በአንዳንድ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት መጓደል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንዳንድ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት መጓደል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ገለጹ፡፡

ተቋማቱ ይህንን ያሉት ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትምህርት ጥራት ላይ ተወያይተዋል።

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ራሳቸውን እንዴት ማዘመን ይችላሉ፣ የጥናትና ምርምር ስራዎችንስ በምን መልኩ መስራት ይኖርባቸዋል የሚሉትና ሌሎችም በውይይቱ የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።

በውይይቱ እንደተመላከተው ተቋማቱ ባለፉት ዓመታት በቁጥር ደረጃ ቢጨምሩም፤ ጥራትና አግባብነት ላይ ውስንነት ይታይባቸዋል።

ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት አጀንሲ የተገኘው መረጃ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር 278 መድረሱን ያሳያል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ እንደተናገሩት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት የጥራት መጓደል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

“አንዳንድ ተቋማት ከ10ኛ ክፍል ላቋረጡ ተማሪዎች ዲግሪ ይሰጣሉ፤ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ሰዎችም እንዲሁ ወረቀት እየወሰዱ ነው” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

መቁረጫ ነጥብ ሳያሟሉ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ መኖራቸው መረጋገጡን ያነሱት ዶክተር አንዱዓለም እውቅና ሳይሰጣቸው እንደሚያስተምሩና ከተፈቀደው ተማሪ ቁጥር በላይ እንደሚመዘግቡም ተናግረዋል።

ችግሮች እርምጃ በመውሰድ ብቻ ስለማይፈቱ ተቀራርቦ በመስራትና በመደጋገፍ ለማስተካከል መስራት ይገባል ብለዋል።

ዶክተር አንዱዓለም ተቋማቱ ከሕገወጥ እንቅስቃሴ ተቆጥበው ወደ ትክክለኛው መስመር መግባት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ተቋማቱ የትምህርት ጥራት ችግር ተብለው ከተለዩት መካከል መምህራንን በጥራት በማቅረብ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

መንግስትና የግሉ ዘርፍ በመቀናጀት ችግሮችን ለማቃለል ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት።

ሚኒስቴሩ የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ በፖሊሲና ስትራቴጂዎች እንደሚያግዛቸውም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሞላ ጸጋዬም ተቋማቱ ጥራታቸውን እንዲያሻሽሉ ከሚመለከታቸው አካላት የሚሰጠው ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።

በተለይም የመምህራን ስልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ ይደረግልን ሲሉ የጠየቁት ፕሬዚዳንቱ ተቋማቱም ራሳቸውን ለማብቃት ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.